ሴቶች 'ፌሚኒስት' መባልን ለምን ይጠላሉ?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጾታ እኩልነት ጥያቄዎች ገፍተው ወደ አደባባይ እየመጡ ነው። በተለይም በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ጉዳዩ ሰፊ ትኩረትና ሽፋን አግኝቷል። ያም ኾኖ ብዙ ሴቶች 'ፌሚኒስት' መባልን አይሹም።

በአሜሪካና በእንግሊዝ በተደረጉ ተከታታይ የዳሰሳ ጥናቶች እንኳ ብንመለከት ከአምስት ሴቶች አንዷ ብቻ 'ፌሚኒስት' መባልን ትሻለች።

ያም ሆኖ በጾታ እኩልነት የሚያምኑ ሴቶች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው።

ሴቶችን አንድ ያደረጉ ንቅናቄዎች

በቅርብ ዓመታት ውስጥ ጾታዊ ንቅናቄዎች ዓለምን ከዳር እስከ ዳር አነቃንቀዋል። ዶናልድ ትራምፕ በ2017 ሥልጣን ሲይዙ ሚሊዮኖች አደባባይ ወጥተው ተቃውመዋቸዋል። የሰልፉ ዓላማ አደጋ ላይ ወድቆ የነበረውን የሴቶች መብትን መከላከል ነበር።

በሆሊውድ የሃርቬይ ዌንስን ቅሌት 80 ሴቶች ድምጻቸውን ካሰሙ በኋላ ዓለም 'ሚ ቱ' በሚለው ንቅናቄ ተናውጦ ነበር። ተዋናይት አሊሳ ሚላኖ ጥቃት የደረሰባችሁ ሁሉ 'እኔም ተጠቅቻለሁ" በሉ ካለች ወዲህ በ24 ሰዓታት ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ሴቶች ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህ ቁልፍ ቃል በ80 አገራት መጠነ ሰፊ ንቅናቄን ፈጥሯል።

ከዚህ ክስተት በኋላ በርካታ ሴት ተዋንያን ፌሚኒስት መሆናቸውን ይፋ አደረጉ። ያም ሆኖ ጥናቶች አሁንም የሚበዙ ሴቶች 'ፌሚኒስት' የሚለው ቃል እንደሚጎረብጣቸው ነው።

አሐዞች ምን ይናገራሉ?

በ2018 በተደረገ አንድ ጥናት 34 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ፌሚኒስት ነን ሲሉ ተናግረዋል። ይህ አሐዝ በ2013፣ 27 በመቶ ብቻ ነበር። በቅርብ ዓመታት ወደ አደባባይ የወጡ የጾታ እኩልነት ንቅናቄዎች ያመጡት ለውጥ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።

አሐዙ በአውሮፓ አገራት መካከል እንኳ ሰፊ ልዩነት እንዳለ ያሳያል። መጠይቅ ከተደረገላቸው የጀርመን ሴቶች 8 ከመቶ ብቻ 'ፌሚኒስት' ነን ሲሉ በአንጻሩ 40 እጅ የሚሆኑት የስዊድን ሴቶች 'ፌሚኒስት' ስለመሆናቸው በኩራት ተናግረዋል።

ዋናው የጥናቱ ጭብጥ ስለምን ሴቶች 'ፌሚኒስት' መባልን ጠሉ የሚለው ነው። የጥናቱ አስገራሚ ገጽታ ደግሞ ራሳቸውን ፌሚኒስት ብለው መጥራት የማይወዱ ሴቶች ብዙዎቹ በጾታ እኩልነት የማያወላዳ አቋም ያላቸው መሆኑ ነው።

43 በመቶ እንግሊዛዊያን፡ "ሴቶች ቤት መዋል አለባቸው"

27 ሺህ ሰዎች የተሳተፉበትና በ2016 በአሜሪካ የተደረገ ሌላ ጥናት ከተጠያቂዎች ሁለት እጅ የሚሆኑ በጾታ እኩልነት የሚያምኑ ሆነው ተገኝተዋል። በ1977 ይህ አሐዝ አንድ አራተኛ ብቻ ነበር።

በተመሳሳይ በ2017 በእንግሊዝ በተደረገ ሌላ ጥናት ከመቶ ስምንት እጅ የሚሆኑት ብቻ የሴቶች ሚና በቤት ውስጥ መወሰን ይኖርበታል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ሴቶች ልጅ በማሳደግና ምግብ በማብሰል መወሰን አለባቸው ብለው የሚያምኑ ዜጎች ቁጥር በ1984 ዓ.ም 43 ከመቶ ደርሶ እንደነበር ማስታወስ ያሻል። ይህ አሐዝ የሚነግረን በዓመታት ውስጥ ትልቅ የአመለካከት ለውጥ መምጣቱን ነው።

ጥያቄው አሁንም በዚህ ሰፊ የአስተሳብ ሽግግር በተደረገበት ዘመን እንኳ 'ፌሚኒስት' መባል የማይወዱ ሴቶች ቁጥር ለምን ከፍተኛ ሆነ የሚለው ነው።

ቃሉ አሉታዊ ገጽታንተላብሷል

በ2018 በተሠራ ሌላ የዳሰሳ ጥናት ከፍ ባለ የቢሮ ሥራ ላይ ያሉት ራሳቸውን 'ፌሚኒስት' ብለው ለመጥራት አያፈገፍጉም። ነገር ግን ዝቅተኛ ሥራ ላይ በተሠማሩት መሀል ቃሉ እምብዛምም አይወደድም።

ሌላ ጥናት እንዳሳየው ደግሞ ፌኒዝም በነጮች ዘንድ ካልሆነ በሂስፓኒክ፣ በእሲያና በጥቁሮች ዘንድ ጥሩ ስም የለውም።

ሦስት እጅ የሚሆኑ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ ሴቶች ፌሚኒዝም የነጭ ሴቶችን ሕይወት ያሻሻለ ነገር አድርገው ነው የሚወስዱት።

ሌላው ለቃሉ አለመወደድ ምክንያት ተደርጎ በጥናት የተወሰደው ነባር አስተሳሰቦች ለውጥ አለማሳየታቸው ነው።

ስካርሌት ከርቲስ በቅርብ ባሳተመችው ''Feminists Do not Wear Pink and Other Lies" በተሰኘው መጽሐፏ እንዳሰፈረችው ፌሚኒስቶች በ1920ዎቹ ትዳር ያልቀናቸው፣ ወንድ ጠል፣ በወሲብ ምርጫቸውም አፈንጋጭ፣ እንዲሁም ወንዳወንድ ተደርገው ይታሰቡ እንደነበረና ይህ አስተሳሰብ ከመቶ ዓመት በኋላም እንዳልተቀረፈ ታስረዳለች።

በዳሰሳ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ ብዙዎቹ ሴቶችም ራሳቸውን 'ፌሚኒስት' ከሚል ቃል ማራቅ የሚሹት ሰዎች ከላይ በተጠቀሱት አሉታዊ መገለጫዎች የተነሳ ነው።