ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጋና በቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ሲፈፅሙ የታዩ ሁለት መምህራን ከሥራቸው ታገዱ
ወሲባዊ ትንኮሳ ሲፈፅሙ በቢቢሲ ጋዜጠኞች በድብቅ የተቀረፁት ጋናውያን መምህራን ከሥራቸው ታግደው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው።
በጋና ዩኒቨርሲቲ መምህራን የሆኑት ፕሮፌሰር ራንስፎርድ እና ዶክተር ፖል ክዋሜ ቡታኮር 'ሴክስ ፎር ግሬድ' የተሰኘው የምርመራ ዘገባ ላይ እንደተማሪ ሆነው በቀረቡት ሪፖርተሮች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ሲፈፅሙ ተቀርፀዋል።
አጣሪ ኮሚቴው ማስረጃዎቹን ከማጋለጡ በፊት ድርጊታቸውን እንዲያምኑ ለፕሮፌሰር ግያምቦ እና ዶክተር ቡታኮር የጋና ዩኒቨርሲቲ ጥሪ አቅርቦ ነበር።
ይሁን እንጂ ሁለቱም የዩኒቨርሲቲው መምህራን፤ ፕሮፌሰር ግያምቦ እና ዶክተር ቡታኮር "ድርጊቱን አልፈፀምንም" ሲሉ ውንጀላውን ተቃውመውታል።
በተመሳሳይ በዚሁ የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ላይ በድብቅ የተቀረፁት በናይጄሪያ የሚሰሩ መምህራንም ከሥራቸው መታገዳቸው ይታወቃል።
በናይጄሪያ ሌጎስ ዩኒቨርሲቲ ፣ ዶክተር ቦኒ ፌስ ኢግቤኔጉ እና ዶክተር ሳሙዔል ኦላዲፖ የተባሉት ሁለት መምህራንን ከሥራቸው ያገደ ሲሆን ይህንኑ የሚመረምር ኮሚቴ አቋቁሟል።
በቢቢሲ 'አፍሪካ አይ' የምርመራ ዘገባ ጋዜጠኞች ቡድን የተሠራው እና በምዕራብ አፍሪካ በሴት ተማሪዎች ላይ በመምህራን የሚፈፀመውን ወሲባዊ ትንኮሳና ጥቃት የሚያሳየው ዘጋቢ ፊልም ሰኞ እለት ተላልፏል።
ዘጋቢ ፊልሙ ከተላለፈ በኋላ በጋና ዩኒቨርሲቲ ፀረ ወሲባዊ ጥቃት ኮሚቴ ኃላፊ በፊልሙ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ሲፈፅሙ የሚታዩትን መምህራን አውግዘዋል።
"ተቀባይነት የሌለው፣ ያሉበትን ኃላፊነት በመጠቀም ያሳዩት ያልተገባ ባህሪ" ሲሉ ነበር ዶክተር ማርጋሬት አሞኮሄኔ ለቢቢሲ የተናገሩት።
ኮሚቴው እያካሄደ ያለው ምርመራ ሲጠናቀቅም ለዩኒቨርሲቲው ባለሥልጣናት እንደሚያሳውቁ የገለፁት የኮሚቴው አስተባባሪ ዶክተር ማርጋሬት፤ "አሁን ላይ እያደረግን ያለነው፤ ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁን የተለያየ ጥቃት የተፈፀመባቸው ተማሪዎች መጥተው ገጠመኛቸውን እንዲያካፍሉን በራችንን መክፈት ነው፤ መጥተው የደረሰባቸውን እንዲነግሩን ጋብዘናቸዋል" ሲሉ አክለዋል።
ማክሰኞ እለት ባወጡት መግለጫ ላይም የጋና ዩኒቨርሲቲ፤ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ትንኮሳዎችንና ጥቃቶችን ሪፖርት የሚያደርጉበት [email protected]. የተሰኘ የኢ ሜይል አድራሻን ጨምሮ 'ተጨማሪ መረጃ የመለዋወጫ ዘዴ' መፍጠራቸውን አስታውቀዋል።
የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ የተሠራው በምዕራብ አፍሪካ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ሲሆን፣ መምህራኖች የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ወሲብን እንደመደራደሪያነት እንደሚያቀርቡ ያሳያል።