ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወሲባዊ ትንኮሳ ያደረሰባት አለቃዋን በማጋለጧ የታሠረችው ሴት
አንዲት ኢንዶኔዥያዊት አለቃዋ ወሲባዊ ትንኮሳ እንደሚያደርስባት ለማሳየት የስልክ ንግግራቸውን ቀድታ ይፋ በማውጣቷ የስድስት ወር እሥር ተፈረደባት።
ባይቅ ኑሪ ማንኩን የተባለችው ሴት፤ ለኢንዶኔዥያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብትልም ተቀባይነት አላገኘችም። ፍርድ ቤቱ "ጨዋነት የጎደለው" ድምጽ በማሰራጨት ጥፋተኛ ያላት ሲሆን፤ የመብት ተሟጋቾች የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ኮንነዋል።
የመብት ተሟጋቾች ውሳኔው ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር በመግለጽ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው። ውሳኔው በመላው ኢንዶኔዥያም ቁጣን ቀስቅሷል።
'ሌጋል ኤድ ፋውንዴሽን ፎር ዘ ፕረስ' የተባለ የመብት ተሟጋች ተቋም ዋና ኃላፊ አዴ ዋሂዲን፤ "ይህ ውሳኔ ወሲባዊ ጥቃት የሚያደርሱ ግለሰቦች ተጠቂዎችን ጥፋተኛ እንዲያደርጉ በር ይከፍታል ብለን እንሰጋለን" ሲሉ ለሮይተርስ ተናገረዋል።
ባይቅ ትሠራበት የነበነረው ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኝ ኃላፊ ወሲባዊ ትንኮሳ እንዳደረሰባት በተደጋጋሚ ተናግራለች። ተገቢ ያልሆነ የሰልክ ጥሪ ያደርግላት እንደነበርም ገልጻለች።
ስልክ ሲደውልላት ድምፁን ለመቅዳት የወሰነችውም ለዚሁ ነበር። አለቃዋ ያልተገቡ የወሲብ ይዘት ያላችው ንግግሮችን አድርጎ ነበር።
የድምፅ ቅጂው በትምህር ቤቱ ሠራተኞች ዘንድ ተሰራጭቶ ለትምህርት ተቋማት ዋና መሥሪያ ቤትም ተሰጥቷል። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይም ተሰራጭቷል። ቅጂው ከተሰራጨ በኋላ ግለሰቡ ከሥራው የተባረረ ሲሆን፤ ባይቅ ላይ ክስ መስርቷል።
ምንም እንኳን ተጎጂዋ ባይቅ ብትሆንም፤ የኢንዶኔዥያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የኢንዶኔዥያን የኤሌክትሮኒክ መረጃ ልውውጥ ሕግ አጣቅሶ ጥፋተኛ ብሏታል።
የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ አብዱላህ "ጥፋተኝነቷ ስለተረጋገጠ ይግባኙ ተቀባይነት አላገኘም" ብለዋል።
ባይቅ የ35,200 ዶላር ቅጣትም ተጥሎባታል።
ባይቅ፤ ቅጂውን ያሰራጨችው እሷ ሳትሆን ጓደኛዋ እንደሆነች በመናገር ተከራክራለች። ጠበቃዋ ጆኮ ጃማዲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ባይቅ ፍርዱን ብትቀበልም፤ "ስለ ወሲባዊ ጥቃት በአደባባይ በመናገሯ የምትቀጣ የመጨረሻዋ ሴት እንደምትሆን ተስፋ ታደርጋለች" ብለዋል።
ከዚህ በኋላ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ይግባኝ ማለት ባይቻልም፤ የኢንዶኔዥያ ፕሬዘዳንት ጆኮ ዊዶዶን ይቅርታ መጠየቅ እንደሚቻል የሕግ አማካሪዎቿ ተናገረዋል።
ፕሬዘዳንቱ ፍርድ ቤት ይግባኟን ካልተቀበለ ምሕረት እንደሚያደርጉላት ቢናገሩም፤ ባይቅ አንዳችም ጥፋት ስለሌለባት ይቅርታቸውን እንደማትሻ ጠበቆቿ ተናግረዋል።