ሕንድ ውቅያኖስ፡ የደቡብ አፍሪካ ባሕር ጠላቂዎች አስክሬን ፍለጋ ላይ ሊሰማሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, Twahir H.Kassim
ከኬንያ ሞምባሳ ወደብ ወደ ባህር ዳርቻው የእቃና የሰው ማሻገሪያ መርከብ ላይ ሆኖ ሲያቋርጥ ሕንድ ውቅያኖስ ውስጥ የገባውን መኪና መፈለግ ከተጀመረ ዘጠኝ ቀናት ተቆጥረዋል።
መኪናው ውስጥ እናት እና ሕፃን ሴት ልጇ እንደነበሩ ተረጋግጧል።
በእቃና ሰው ማሻገሪያ መርከብ ላይ ተጭነው ከሞምባሳ ወደ ሊኮኒን በማቋረጥ ላይ ሳሉ መሃል ላይ ሲደርስ መኪናው ወደ ኋላ በመንሸራተቱ አደጋው እንዳጋጠመ ታውቋል።
አደጋው ሲደርስ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት ተሠራጭቷል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
አደጋው ካጋጠመበት እለት አንስቶ የግለሰቦቹን አስክሬን ለመፈለግ በርካታ ድርጅቶች ተሰማርተው ጥረት ሲደረግ ቢቆይም አስክሬናቸውም ሆነ መኪናው ሊገኝ አልቻለም። ይህም በበርካቶች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል፤ በኬንያ የባህር ኃይል የነፍስ አድን መሳሪያ በቂ ባለመሆኑ ምክንያት በድርጅቱ ላይም ጥቁር ጥላን ጥሎ አልፏል።
በመሆኑም ኬንያ የሰጠሙትን ሰዎች አስክሬን ለመፈለግ ደቡብ አፍሪካ ባሕር ጠላቂዎች ላይ ተስፋ ጥላለች።
የመንግሥት ቃል አቀባይ ሲይረስ ኦጉና፤ ደቡብ አፍሪካዊያን ባህር ጠላቂዎች ለፍለጋው በሁለት ቡድን ተከፍለው እንደሚገቡ ተናግረዋል። ፍለጋውንም ነገ እንደሚጀምሩ በመግለፅ።
"የመጀመሪያው ባህር ጠላቂዎች ቡድን ትናንት ኬንያ የደረሰ ሲሆን ሁለተኛ ቡድን ዛሬ ገብቷል፤ ፍለጋቸውን ለመቀጠልም ከኬንያ የፍለጋ ሠራተኞች ጋር ይገናኛሉ" ሲሉ ቃል አቀባዩ ለስታር ጋዜጣ ተናግረዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ጀምስ ማቺሪያም ባህር ጠላቂዎቹ ኬንያ መድረሳቸውን ለጋዜጠኞች አረጋግጠዋል።
"ከስዊድን ባለሙያ አለን፤ የአደጋ ሠራተኞችን እንዲቀላቀሉ ደግሞ ሌሎች ባለሙያዎችን ከደቡብ አፍሪካ ጨምረናል" ብለዋል።
አደጋው በዚህ ዓመት ሃገር አቀፍ የጀግኖች ቀንን ለማክበር በዚያው የእቃና የሰው ማጓጓዣ መርከብ ማቋረጫ አቅራቢያ ይካሄዳል በተባለው ዝግጅት ላይ መጥፎ ጥላ አጥልቶበታል።
በአስር ቀናት ውስጥ 'ማማ ጊና ዋተር ፍሮንት መናፈሻ' ለሚካሄደው ዝግጅት የኬንያ የባህር ኃይል ቡድን የመርከብና ሄሊኮፕተር ትዕይንት ለማቅረብ ልምምድ እያደረጉ ይገኛሉ።













