ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሃጃር ሬይሶኒ፡ በፅንስ ማቋረጥ ምክንያት ለእስር የተዳረገችው ሞሮኳዊቷ ጋዜጠኛ
ሞሮኳዊቷ ጋዜጠኛ ከጋብቻ ውጭ ወሲብ ፈፅመሻል፣ እንዲሁም ፅንስ አቋርጠሻል ተብላ የአንድ ዓመት እስር ተፈርዶባታል። የመብት ተሟጋቾች ጉዳዩን ጋዜጠኞችን የማፈን አንዱ ሰበብ ነው ሲሉ አውግዘውታል።
ሃጃር ሬይሶኒ ባሳለፍነው ነሐሴ ወር ከእጮኛዋ ጋር ሆና ከማሕፀንና ፅንስ ክሊኒክ ሲወጡ ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለችው።
የ28 ዓመቷ ጋዜጠኛ ሃጃር፤ "ድርጊቱን አልፈፀምኩም፤ ወደ ሕክምና ተቋሙ ያመራሁት የደም መፍሰስ የጤና እክል ስላጋጠመኝ ነው" ስትል ክሱን ተቃውማለች።
ሃጃር በአገሪቷ ለሚገኘው ገለልተኛ ጋዜጣ የምትሠራ ሲሆን የመንግሥት ባለሥልጣናትንም በመተቸት ትታወቃለች።
በአክሀበር አል ያኦም ዴይሊ የምትሠራ ጋዜጠኛ በሃጃር ላይ የተሰጠውን ፍርድ "የፖለቲካ እስር" ነው ስትል አውግዛዋለች። ምክንያቷን ስታስረዳም ሃጃር በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ ስለቤተሰቧ እና ስለጽሁፎቿ በፖሊስ መጠየቋን ትገልፃለች።
ጥቁር ሰደርያና ጭንቅላቷን ሸፍና በሞሮኮዋ መዲና ራባት ፍርድ ቤት የቀረበችው ጋዜጠኛዋ፤ እሷ እና ሱዳናዊው እጮኛዋ የፅንስ ማቋረጥዘ አልፈፀምንም ሲሉ ክሱን ተቃውመዋል።
የጋዜጠኛዋ ጠበቃ አብደልሞላ ኢል ማሮሪ በበኩላቸው "በዚህ ፍርድ ሁላችንም ደንግጠናል" ሲሉ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል። አክለውም "ሁሉም የሕክምናና የሕግ ማስረጃዎች ነፃ እንድትወጣ ማድረግ ነበረባቸው፤ ግን አልሆነም" በማለት ይግባኝ እንደሚሉ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ አቃቤ ሕጉ ጋዜጠኛዋ በሥራዋ ምክንያት አለመታሰሯን ገልፀው፣ የታየችበት የጤና ተቋም ሕገ ወጥ ፅንስ ማቋረጥ ያካሂዳል በሚል በፖሊስ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን ገልፀዋል።
ፍርድ ቤቱ እጮኛዋን የአንድ ዓመት እንዲሁም ሐኪሟ ላይ የሁለት ዓመት እስራት በይኖባቸዋል። በጤና ተቋሙ የነበሩ የሐኪሟ ረዳትና ነርስ ጥፋተኛ የተባሉ ቢሆንም በተሰጣቸው ጊዜ ከምንም ዓይነት ወንጀል ራሳቸውን እንዲያቅቡ እገዳ ተጥሎባቸዋል።
በአካባቢው በሂዩማን ራይትስ ዋች ዳይሬክተር የሆኑት አህመድ በንቸምሲ "ፍርዱ በሞሮኮ ላለው ነፃነት ጥቁር ቀን ሆኗል" ሲሉ ኮንነውታል። ጉዳዩ ኢፍትሐዊነት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የግለሰቦችን ነፃነት መጋፋት ነው ብለውታል።