ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዌልስ፡ ከልጁ ስድስት ልጆች የወለደው አባት ፍርድ ቤት ቀረበ
በደቡብ ምዕራብ ዌልስ፤ ከራሱ ልጅ ስድስት ልጆች የወለደውና 23 ጊዜ በመድፈር የተከሰሰው ግለሰብ ክስ ተመሰረተበት።
የተከሳሹ ግለሰብ ድርጊት ለነጋሪም ለሰሚም ግራ ነው። የልጅ ልጁን [የራሱን ልጅ] እና ሌሎች ሴት ልጆቹንም በመድፈርም ክስ ቀርቦበታል።
ግለሰቡ ግን የቀረቡበትን 36 የአስገድዶ መድፈር ክሶች "አላደረኩትም" ሲል ተቃውሟል።
አቃቤ ሕጉ ጆን ሂፕኪን እንዳሉት ግለሰቡ ተጠቂዎቹን ያግባባቸው ነበር።
ለፍትሕ ሂደቱ ሲባል ስሙ እንዲጠቀስ ያልተፈለገው ተከሳሹ፤ ሴቶቹ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በምስጢር በኢሜይል መልዕክት ይልክላቸው እንደነበር አቃቤ ሕግ አክሏል።
አቶ ሂፕኪን "በሦስቱ ልጆቹ ላይ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ አድርጓል፤ ይህንን ሁሉ ወንጀል ለመፈፀምም ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ፣ አዕምሯቸውን በማሳመንና የማታለያ ዘዴዎችን ተጠቅሟል" ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
"የሴቶቹ ፍላጎታቸው በሙሉ የተፃፈው በእርሱ ነው" የሚሉት አቃቤ ሕጉ፤ ግለሰቡ በጥንቆላና ሚስጥራዊነት በተሞላበት መልኩ የማይዳሰስ እና የማይጨበጥ ሐሰተኛ ዓለምን ፈጥሮላቸዋል።
ምስጢሩ በተጠበቀ መልኩ የኢሜል መልዕክቶችን በመላክ እያዘዛቸው ወሲብ እዲፈፅሙ ያታልላቸው እንደነበርም ያስረዳሉ።
ግለሰቡ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ወሲባዊ ፍላጎቱን ለማርካት እንዲፈቅዱለት ለማድረግ እንደሆነም ተነግሯል።
የዌልስ ሳዋንሲ ክራውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ለመስጠት የሦስት ሳምንታት ቀጠሮ ሰጥቷል።