ያሳደጋቸው ሦስት ልጆች የእራሱ አለመሆናቸውን ያወቀው እንግሊዛዊ ቱጃር

"በመዶሻ የተመታሁ የክል ነው የተሰማኝ።" በማለት ነበር የ54 ዓመቱ ቱጃር መውለድ እንደማይችል ሲነገረው የተሰማውን ስሜት የገለጸው።

ባለጸጋው ሪቻርድ ሜሰን 'ሲስቲክ ፋይብሮሲስ' የተሰኝ የጤና ችግር እንዳለበት ከሁለት ዓመት በፊት ነበር የተነገረው። 'ሲስቲክ ፋይብሮሲስ' የሚጠቁ ከ97-98 በመቶ መውለድ አይችሉም።

ሪቻርድን ለከፍተኛ ደንጋጤ የዳረገው ግን በዘር በሚተላለፈው በሽታ 'ሲስቲክ ፋይብሮሲስ' መያዙን ማወቁ አልነበረም።

የሶስት ልጆች አባት ነኝ ብሎ የሚያስበውን አባት ክፉኛ ያስደነገጠው ግን ከልጅነቱ ጀምሮ መሃን እንደሆነ ማወቁ ነበር።

ሪቻርድ አንድ እውነታ ተገልጦለታል። ይህም ከቀድሞ ሚሰቱ ወልጃለሁ ብሎ ያሰባቸው ሦስቱ ልጆቹ የእርሱ አለመሆናቸውን። "'ሲስቲክ ፋይብሮሲስ' ያለባቸው ወንዶች በሙሉ መሃን መሆናቸውን እና የመውለድ እድላቸውም ዝቅተኛ መሆኑ ነው ሃኪሞች የነገሩኝ" በማለት ለቢቢሲ ሬድዮ ፋይቭ ላይቭ ተናግሯል።

"ዶክተሮቹ ተሳስተው መስሎኝ ነበር። እነርሱ ግን እርግጠኛ መሆናቸውን እና የቅድሞ ባለቤቴን ማነጋገር እንደሚኖርብኝ መከሩኝ"

ሪቻርድ ከአዲሷ ባለቤቱ ኤማ ጋር መውለድ ሲያቅታቸው ነበር ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ያቀኑት።

ሪቻርድ ከቅድሞ ባለቤቱ ኬት ጋር ፍቺ የፈጸሙት ከ20 ዓመታት የጋብቻ ህይወት በኋላ ነበረ። በህክምና ውጤት ግራ የተጋባው ሪቻርድ የቀድሞ ባለቤቱን በጉዳዩ ላይ ያነጋግራታል።

የቀድሞ የትዳር አጋሩም የ19 ዓመት መንታዮቹ ኤድ እና ጆኤል የ23ዓመቱ ታላቃቸው ዊሌም ጭምር ልጆቹ እንደሆኑ ተትነግረዋለች። የዘረመል ምርመራው ግን ይህ አለመሆኑን አረጋግጧል።

"ይህ ሁሉ በሚፈጠርበት ጊዜ ጆሮዬ ውስጥ የሚደውልበኝ ነገር ነበር" ብሏል።

"ሁሉም ነገር ግራ አጋባኝ። የአባታቸው ማንነት እንቅልፍ ነሳኝ"

የቀድሞ ባለቤቱ ከሪቻርድ ጋር ስትለያይ 5 ሚሊዮን ዶላር ወስዳ ነበረ። ሪቻርድ ለተፈጸመበት በደል የቀድሞ ባለቤቱን ፍርድ ቤት ገተራት። ለደረሰበት ጉዳትም 320 ሺህ ዶላር ካሳ እንድትከፍል ፍርድ ቤቱ የወሰነባት ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ ጨምሮም የልጆቹን አባት ማንነት ያለመናገር መብት ፍቅዶላታል።

"የቀድሞ ባለቤቱ የልጆቹን አባት ማንነነት ማሳወቅ አልፈለገችም። ይህ ለምን እንደሆነ አላወቅንም። ለዚህም ነው የገንዘብ ካሳ ለመክፈል የተስማማችው። ፍርድ ቤቱም ይህን መብት ሰጥቷል" በማለት የሪቻርድ የሕግ አማካሪ ሮጀር ቴሬል ለዴይሊ ቴሌግራፍ ተናግሯል ።

"ወደፊት ልጆቹ የአባታቸውን ማንነት ማወቅ መፈለጋቸው አይቀርም። ጊዜው ሲደርስ ደግሞ መረጃው ይኖረኛል። የሰውዬውን ማንነት ማወቅ አልቻልኩም። ከጓደኞቼ መካከል መሆኑን አላውቅም ግን የቅርብ ሰው ሊሆን ይችላል" ይላል ሪቻርድ።

"ልጆቹ ኳስ ሲጫወቱ ከአጠገቤ ሆኖ ሲመለከት የኖረ ሰው ሊሆን ይችላል። ወይም በትምህርት ቤታቸው በሚደረጉ የወላጆች ጥሪዎችም ላይ ተሳታፊ ሆኖ ይሆናል" በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።

አክሎም "እንደዚህ ዓይነት ምስጢር በሕይወት ውስጥ ሲያጋጥምና በተለይ ከባድ ተጽዕኖ ያደረሰ ሲሆን የበለጠ ለማወቅ ያጓጓል" ብሏል።

ሪቻርድ ማሶን የልጆቹን ትክክለኛ አባት ማንነት ለሚነግረው ሰው 6400 ዶላር እንደሚከፍል ተናግሯል።

ዴይሊ ሜል የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ የሪቻርድ የቀድሞ ባለቤት ትሠራበት በነበረው ባርክሌ ባንክ አብሯት ይሠራ ከነበረ ሰው ጋር በተለያዩ ጊዜያት የፍቅር ግንኙነት ጀምረዋል ብሎ የሚገመተው ግለሰብ የልጆቹ አባት ሊሆን እንደሚችል እንደሚጠረጥር ነግሮኛል ሲል ዘግቧል።

ቢቢሲ ኬትን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የግንኙነት መቋረጥ

በክሱ ምክንያት ሁለቱ ልጆች ከሪቻርድ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋርጠዋል።

"እንቅስቃሴያቸውን በሙሉ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ እከታተላለሁ። ታላቁ ልጅ ከቀርብ ጊዜ በፊት ተመረቀ እኔ ግን አልተጠራሁም ነበር። ይህ ደግሞ በጣም ያሳዝነኛል" በማለት ለዴይሊ ሜል ተናግሯል።

ኤድ የተሰኘው ከመንትዮቹ አንዱ ብቻ ነው ከሪቻርድ ጋር ግንኙነት ያለው።

ጆኤል የተሰኘው ከመንትያዎቹ አንዱ ባሳለፍነው ሳምንት ለዴይሊ ሜል ሲናገር የሪቻርድን ውሳኔዎች ተችቷል።

"ሰዎችን የሚጨቁን ሰው ነው። ከእርሱ ጋር ብዙ ጊዜ የማሳለፍ ፍላጎት አይፈጥርም። ከ15 ዓመቴ ጀምሮ ነው ይህ እየታወቀኝ የመጣው" ብሏል።

አክሎም ወላጅ አባቱን የማግኘት ፍላጎት እንደሌለውም ተናግሯል።