ሳናውቀው እያለቁብን ያሉ ስድስት ነገሮች

ምድራችን የውሃ እጥረት ያጋጥማታል አልያም ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች እያለቁ ነው የሚሉ ዜናዎችን ሰምተን ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሳናስተውለው ያለአግባብ እየተጠቀምናቸው የሚገኙ ብዙ የተፈጥሮ ሃብቶች አሉ።

ከእነዚህ መካከል ስድስቱ ብዙም ትኩረት ያልተሰጣቸው ይመስላሉ።

1. የምህዋር ነጻ ቦታ

እ.አ.አ. በ 2019 ብቻ ከ500 ሺ በላይ የተለያዩ ቁሶች በምድር ምህዋር ዙሪያ እንደሚሽከረከሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

ከቁሶቹ መካከል ደግሞ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት 2 ሺ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። የዕለት ተዕለት ግንኙነታችንን ለማቀላጠፍ፣ አቅጣጫ ለማወቅ፣ ኢንተርኔት ለመጠቀምና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች የምንጠቀምባቸው ሳተላይቶች ናቸው እነዚህ።

የተቀሩት (498 ሺ) የሚሆኑት ደግሞ የተለያዩ ሮኬቶች ስብርባሪና በተለያዩ አጋጣሚዎች ሳተላይቶችና መሰል ቁሶች ሲጋጩ የሚቀሩ ስብርባሪዎች ናቸው።

ይህ ቁጥር ምናልባት ከዚህም በላይ ከፍ የማለት እድሉ ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም በየቀኑ የተለያዩ ሳተላይቶች ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ይመጥቃሉ።

እነዚህ ትርፍራፊ ቁሶች ከጊዜ ብዛት በእጅጉ ተጠራቅመው ምህዋራችንን ማጨናነቅ ከጀመሩ የሰነባበቱ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሁሉ ነገራችንን መሰረት ያደረግንበት ኢንተርኔት ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል።

2. አሸዋ

ምናልባት በጣም ብዙ የዓለማችንን ክፍል ሸፍኖ የሚገኘው አሸዋ እንዴት ነው ሊያልቅ የሚችለው ብላችሁ ልታስቡ ትችላላችሁ። ነገር ግን ጉዳዩ ሌላ ነው።

አንድ የተባበሩት መንግስታት የሰራው ጥናት እንደሚያሳየው አሸዋ በጣም በፍጥነት እየተጠቀምናቸው ከሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶች መካከል አንዱ ነው። አሸዋ በብዙ ሺህ ዓመታት ሂደት የሚፈጠር ሲሆን አጠቃቀማችን ግን አሳሳቢ ነው ይላል ጥናቱ።

አሸዋ ለትላልቅ ግንባታዎች፣ ጉድጓዶችን ለመሙላት፣ የውሃ ላይ ከተሞችን ለመስራት፣ ውሃ ለማጣራት እንዲሁም በየቤታችን የሚገኘውን መስታወት ለመስራት አገልግሎት ላይ ይውላል።

3. ሂሊየም

ሂሊየም ከከርሰ ምድር የሚወጣ አላቂ የተፈጥሮ ሃብት ነው። አሁን ባለው የሰው ልጆች አጠቃቀም ደግሞ በመጪዎቹ ከ60 እስከ 80 ባሉት ዓመታት ውስጥ ሂሊየም የሚባል ነገር አይኖርም ማለት ነው።

እንደውም አንዳንድ ባለሙያዎች ሂሊየም ከ30 እስከ 50 ባሉት ዓመታት ከምድረ ገጽ ስለመጥፋቱ ደርሰንበታል እያሉ ነው።

ሂሊየም ለልደትና ለተለያዩ ዝግጅቶች የምንጠቀምባቸውን ፊኛዎች ለመወጠር ባለፈ በህክምናው ዘርፍም ብዙ ግልጋሎቶችን ይሰጣል። ኤምአርአይ ተብሎ የሚጠራው ዘመን አመጣሹ የህክምና ምርመራ መሳሪያ ያለ ሂሊየም ማሰብ ከባድ ነው።

ምክንያቱም የመሳሪያውን ማግኔቶች ለማቀዝቀዝ ስለሚያገለግል ነው።

4. ሙዝ

ምድራችን ሙዝ የማይበቅልባት ሆና ማሰብ ከባድ ነው።

አብዛኛው ለሽያጭ የሚቀርበውና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚበቅለው የሙዝ አይነት 'ፓናማ ዲዚዝ' በተባለ የፈንገስ አይነት አማካኝነት ትልቅ ጋሬጣ ተደቅኖበታል።

በብዛት ለምግብነት የሚውለው የሙዝ ዘር 'ካቬንዲሽ' የሚባለው አይነት ሲሆን ፓናማ ዲዚዝ የተባለው ፈንገስ በቀላሉ ተሰራጭቶ ከምድረ ገጽ ሊያጠፋው ተቃርቧል እየተባለ ነው።

ከዚህ በፊት እ.አ.አ. በ1950ዎቹ አካባቢ ይሄው በሽታ የሙዝ ምርት ላይ ጥፋት አስከትሎ ነበር። ሙዝ ጠፍቷል በሚባልበት ደረጃ ላይ ተደርሶም ነበር። በጊዜው የነበሩት የሙዝ አምራቾች በዚሁ ምክንያት ነው 'ግሮስ ሚቸል' የሚባለውን የሙዝ ዘር ትተው አሁን በብዛት ለምግብነት የሚውለውን 'ካቬንዲሽ' መጠቀም የጀመሩት።

በአሁኑ ሰአት የዘርፉ ተመራማሪዎች ፓናማ ዲዚዝ የሚባለውን ፈንገስ መቋቋም የሚችልና ለምግብነት የሚውል የሙዝ አይነት ለማግኘት እየሰራን ብለዋል።

5. አፈር

ምንም እንኳን በምድራችን ላይ ያለው የአፈር መጠን በድንገት የሚያልቅ ነገር ባይሆንም አሳሳቢ በሚባል ደረጃ በሰው ልጆች ያለአግባብ አጠቃቀም ምክንያት እየተበዘበዘ ይገኛል።

የአፈር የላይኛው ክፍል አብዛኛዎቹ ተክሎች ለእድገታቸው የሚያስፈልጓቸውን ንጥረ ነገሮች የሚያገኙበት ሲሆን ይህ የላይኛው ክፍል በእጅጉ እየተጎዳ ነው።

' WWF' የተባለ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ላይ የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ዓለማቀፍ ድርጅት እንዳስታወቀው ባለፉት 150 ዓመታት ብቻ ግማሽ የሚሆነው የዓለማችን የላይኛው የአፈር ክፍል ጠፍቷል።

ነገሮችን አስፈሪ የሚያደርገው ደግሞ አፈር ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ዝግጁ እስከሚሆን 500 መፍጀቱ ነው።

ከፍተኛ የግብርና ስራዎች፣ የደኖች መጨፍጨፍ፣ የዓለም ሙቀት መጨመርና ጎርፍ የዓለማችንን የአፈር የላይኛውን ክፍል በእጅጉ እየጎዱ ያሉ ነገሮች ናቸው።

6. ፎስፍረስ

ብዙ ሰዎች ፎስፈረስ በዕለት ተዕለት ኑሯችሁ ውስጥ አገልግሎቱ ምንድነው ቢባሉ መልሳቸው ምንም እንደሚሆን አያጠራጥርም።

ከየትኛውም አይነት ሰው ቤት የማይጠፋው ክብሪት የሚሰራው ከፎስፍረስ መሆኑን ያውቃሉ? ከዚህ በተጨማሪ በሰውነታችን ውስጥ የፎስፍረስ መጠን አነሰ ማለት የዘረመል ስርአታችን ይበላሻል።

በጣም ወሳኝ የሆነውና ሁሉም የዓለማችን ገበሬዎች የሚጠቀሙት ማዳበሪያ ያለ ፎስፍረስ የሚታሰብ አይደለም። ምናልባት ፎስፍረስን በቀጥታ ላንመገበው እንችል ይሆናል፤ ነገር ግን አብዛኛዎቹ በገበሬዎች የሚመረቱ ምግቦች ሁሉ ከፎስፍረስ ጋር ጥብቅ ግንኙነት አላቸው።

አሁን ባለው የፎስፍረስ አጠቃቀማችን በትንሹ ከ35 ዓመት በኋላ ወይም ደግሞ በትልቁ በ400 ዓመታት በኋላ የሚወለዱ ልጆች ፎስፍረስን የሚያውቁት በስም ብቻ ሊሆን ይችላል።