ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የማዉ ጫካን ለማዳን 60 ሺ ኬንያውያን ከመኖሪያቸው ተባረሩ
በኬንያ ተፈጥሯዊ ሃብቶች ዝርዝር ውስጥ እጅግ በጣም ወሳኝ ከሚባለው የማዉ ጫካ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ከ60ሺ በላይ ዜጎችን መንግስት ማባረር ጀምሯል።
የኬንያ ዋነኛ የውሃ ምንጭ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ጫካ የዝናብ ውሃን ለረጅም ጊዜ ይዞ የሚያቆይ ሲሆን በደረቅ ወራት ደግሞ ውሃውን ወደ ሃገሪቱ ብዙ ወንዞች መልሶ ይለቀዋል።
ባለስልጣናት እንደሚሉት ሰዎቹ በሕገ-ወጥ መንገድ የሰፈሩ ሲሆን የእርሻ ቦታ ለማዘጋጀት በማሰብ ጫካውን እየመነጠሩት ነው።
ከሰኞ ጀምሮ አንዳንድ ፍቃደኛ ቤተሰቦች ጫካ ውስጥ የሰሩትን ቤትና ያዘጋጇቸውን የእርሻ ቦታዎች በገዛ ፍቃዳቸው ለቅቀው መሄድ የጀመሩ ሲሆን መንግሥት በኃይል ንብረታችን ከሚያወድም በሰላም ለመልቀቅ መርጠናል ብለዋል።
በአካባቢው የሚገኙ 31 ትምህርት ቤቶችም በዚሁ ምክንያት ከሰኞ ጀምሮ ዝግ ሆነዋል። በዚህም ከ10 ሺ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ቀርተዋል።
የኬንያ የደን አገልግሎት መስሪያ ቤት በመቶዎች የሚቆጠሩ የታጠቁ ጠባቂዎቹን ከፖሊስ ጎን ሆነው ነዋሪዎቹን ከማዉ ጫካ የማስወጣት ስራውን እንዲያግዙ በማለት አሰማርቷቸዋል።
ነዋሪዎቹን የማስወጣት ስራውን እጅግ አስፈላጊ ያደረገው አካባቢው ትልቅ ውሃ የመቋጠር አቅም ስላለውና የዝናብ ዑደትን በእጅጉ ስለሚወስን ነው ብለዋል የሃገሪቱ የአካባቢ ሚኒስትር ካሪያኮ ቶቢኮ።
ከዚህ በተጨማሪ ብዙ ጎብኚዎችን የሚስበውና ብዙ የዱር እንስሳት ወደ ታንዛንያ ሲሄዱ አቋርጠውት የሚያልፉት የማራ ወንዝ ቋሚ የውሃ ምንጭ ነው።
ነገር ግን ይህ የመንግሥት እርምጃ ከአንዳንድ የግዛት አስተዳዳሪዎች ወቀሳን አስከትሏል። መንግሥት ጉዳዩን በድርድርና በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ሲገባው በኃይል እርምጃ መውሰዱ ተገቢ አይደለም ብለዋል።
ጫካው የሚገኝበት ክልል አስተዳዳሪ የሆኑት ኪፕቹምባ ሙርኮመን በበኩላቸው ነዋሪዎቹ ከጫካው ወጥተው እንዳይሄዱ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በቅርብ የሚገኝ አዋሳኝ ክልል አስተዳዳሪ ሌዳማ ኦሌ ኪና ደግሞ በእሱ በኩል ያሉት የማሳይ ማህበረሰብ ነዋሪዎች በሰላም መውጣታቸውን በመግለጽ የማዉ ጫካን የመታደግ ስራው በመጨረሻም ተጀመረ ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
እንደ ዓለማቀፉ የዱር እንስሳት ጥናት ፈንድ መረጃ መሰረት ከሆነ ኬንያ ነጻነቷን ካገኘችበት እ.አ.አ. 1963 ጀምሮ የማዉ ጫካ 37 % የሚሆነውን ሽፋኑን በሰዎች ምክንያት አጥቷል።