ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"በክልሉ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል እናስቆማለን" የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት
በመጪው ዓመት በክልሉ ውስጥ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ አካል እንዳይኖር አደርጋለሁ ሲል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ።
ከመንግሥት ውጪ በሕገ-ወጥ መንገድ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀስ አካል እንዳይኖር ይደረጋል ሲሉ የክልሉ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ አድማሱ ዳምጠው ተናግረዋል።
አቶ አድማሱ ይህን ያሉት ክልሉን የሚያስተዳድረው የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ እና የክልሉ መንግሥት በመጪው አዲስ የሥራ ዘመን ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩባቸው ቁልፍ ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጠኞችን ሰብስበው ዛሬ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው።
ቁጥራቸው እና የታጠቁት መሳሪያ በውል የማይታወቅ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ኃይሎች በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል። ከዚህ ቀደም ኦነግ ታጣቂ ኃይሎቹን እንደማያውቃቸው ያሳወቀ ሲሆን፤ ታጣቂዎቹም ከፓርቲው ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ይፋ አድርገዋል።
በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው ኃይል የጦር መሪ የሆነው ኩምሳ ዲሪባ ወይም መሮ፤ በምዕራቡ ክፍል የሚገኘው ኃይል የትጥቅ ትግል ማድረጉን እንደሚቀጥል በተደጋጋሚ ለቢቢሲ ተናግሯል።
የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በበኩላቸው ኦነግ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ የጦር ኃይል አይኖረውም በማለት ተናግረው ነበር።
አቶ አድማሱ በመጪው ዓመት ሰላምን እና ጸጥታን ማስከበር ዋነኛው የመንግሥት ትኩረት መሆኑን ተናግረዋል።
"ሕግ የሚተላለፍ አካልን ለሕግ እናቀርባለን። ኦሮሚያ ሕግን ተላልፎ መኖር የማይቻልበት ክልል መሆኑን በመጪው ዓመት እናስመሰክራለን።" ብለዋል ቃል አቀባዩ።
የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በክልሉ ውስጥ ለእስር እየተዳረጉ ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ አድማሱ ሲመልሱ፤ "ከዚህ በፊት ሲከናወኑ የቆዩት ሕግን የማስከበር ስራዎች ናቸው" ሲሉ መልሰዋል።
የምርጫ ጉዳይ . . .
በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተ የክልሉ መንግሥትም ሆነ ክልሉን የሚያስተዳድረው ፓርቲ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ ፍላጎት አላቸው ብለዋል።
"ምርጫ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እና ያለ ጸጥታ ችግር እንዲካሄድ ስራዎች ይከናወናሉ" ብለዋል አቶ አድማሱ።
አቶ አድማሱ እንደሚሉት ከሆነ በቀን ለ8 ሰዓት ብቻ በመስራት የህዝቡን ፍላጎት ማሟላት ስለማይቻል የመንግሥት ሰራተኞች በሳምንት ለተጨማሪ አምስት ሰዓታት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ በሳምንት ለተጨማሪ 5 ሰዓት የመስራት ፍላጎቱ የመነጫው ከክልሉ የመንግሥት ሰራተኞች ነው።
የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ግብርና፣ ትምህርት እና የጤና ጉዳዮች ትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።