የሁዋዌ የወደፊት ስልክ የጉግል መተግበሪያዎች ላይኖሩት ይችላል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሁዋዌ በቀጣይ የሚያመርተው ስልክ አቅጣጫ አመላካች (ጉግል ማፕ) እና ዩቲዩብን ጨምሮ ሌሎች የጉግል መተግበሪያዎች ላይኖሩት እንደሚችል ተገለፀ።
የጉግል ኩባንያ፤ የአሜሪካ መንግሥት የሁዋዌ ምርቶች በአገሪቷ እንዳይሸጡ በመከልከሉ ምክንያት መተግበሪያዎቹን ለቻይናው ግዙፍ ስልክ አምራች ድርጅት- ሁዋዌ ፈቃድ መስጠት አልችልም ብሏል።
በዚህም ምክንያት ሁዋዌ በቀጣይ የሚያመርታቸው ስልኮች ላይ የጉግል መተግበሪያን እንዳይጠቀም ያደርገዋል። በመሆኑም የስልኩ ተጠቃሚዎች በጣም አስፈላጊ የሆኑ መተግበሪያዎችን መጠቀም አይችሉም።
ሁዋዌ ያለ ጉግል መተግበሪያዎች ስልኮቹን ለመሸጥ ፈተና ሊያጋጥመው እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የአገሪቷን የደህንነት ጉዳይ በማንሳት፤ የአሜሪካ መንግሥት የአሜሪካ ድርጅቶች የሁዋዌ ምርቶችን እንዳይሸጡም ሆነ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች እንዳይጠቀሙ የከለከለው ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ ነበር። ሁዋዌ ግን ይህንን ክልከላ አልተቀበለውም።
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ወር ክልከላው ሊነሳ እንደሚችል ተናግረው ነበር። ይሁን እንጂ 130 የሚሆኑ ጥያቄዎችን ከመቀበላቸው በስተቀር የአገሪቷ ባለሥልጣናት ከሁዋዌ ጋር ግብይት እንዲደረግ ፈቃድ አልሰጡም።
በእርግጥ የአንድሮይድ መተግበሪያ ማንኛውንም ሶፍት ዌር መቀበል የሚያስችል አሠራር ስላለው ማንኛውም ሶፍት ዌር አምራቾች ለዘመናዊ ስልኮቻቸውም ሆነ ታብሌቶቻቸው ሊያቀርቡላቸው ይችላሉ።
ነገር ግን ይህን የሚያደርጉ ድርጅቶች የተለመዱትን እንደ አቅጣጫ አመላካች (ጉግል ማፕ)፣ የጨዋታ (ጌም)፣ የመፈለጊያ፣ ፎቶግራፎች፣ ፕለይ ስቶር እና ዩቲዩብን ለማካተት ከጉግል ጋር መስማማት ይጠበቅባቸዋል።
ጉግል በበኩሉ መተግበሪያውን ለሁዋዌ ለመስጠት ፈቃድ መጠየቅ፤ አለመጠየቁን በተመለከተ ያለው ነገር የለም።
ሁዋዌም በመግለጫው "የአሜሪካ መንግሥት ከፈቀደልን ሁዋዌ አንድሮይድ ኦ ኤስን እና ምህዳሩን መጠቀሙን ይቀጥላል፤ ካልሆነ ግን የራሳችንን የመገልገያ ዘዴ መሥራታችንን እንቀጥላለን" ብሏል።
ደንበኞቹ ድርጅቱ ከአንድሮይድ ጋር ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች ለማስተናገድም 'ሁዋዌ አንሰርስ' በሚል ድረ ገፅ ከፍቷል።
"የሁዋዌ ምርት የሆነ ዘመናዊ ስልክ የገዙ አሊያም ለመግዛት ያሰቡ፤ ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት ዓለም የሚገለገልባቸውን መተግበሪያዎች መጠቀም ይችላሉ" ብሏል- ሁዋዌ።
"ሁሉም ምርቶቻችን ዋስትና ያላቸው ሲሆን ድርጅቱ ሙሉ የአገልግሎት ድጋፍ ያደርጋል" ሲልም ከደንበኞቹ ጎን እንደሆነ ገልጿል።















