ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከመስመጥ አደጋ የተረፉት ሁለት ኤርትራዊያን ስደተኞች
ኤርትራዊያኑ ስደተኞቹ በኩረፅዮን ፀጋዘዓብና በክሪ መሐመድ አገራቸውን ጥለው የተሰደዱት "ሕይወታችን ይለወጣል" ብለው ነበር።
ሊቢያ ከገቡ በኋላ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከመዲናዋ ትሪፖሊ 120 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ክሆምስ የስደተኛ ማቆያ አሳልፈዋል። እዚያም ከፀሐይ ብርሃን በሚያገኟት ትንሽ ጭላንጭል ውስጥ ተቆልፈው ነበር የቆዩት።
ሕልማቸው የሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ መሻገር ነበር።
በስደተኛ ማቆያው ውስጥ ያሳለፉትን አሰቃቂ ሕይወት ለማምለጥ ጀልባ ላይ ለመሳፈር እንደተገደዱ በኩረፅዮን ይናገራል። ባህሩን እንዲያሻግሯቸውም ለደላሎች ገንዘብ ከፍለዋል። ግን ምን ያህል እንደሆነ አልገለፁልንም።
ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪ ደላሎቹ ጀልባዋ በምሽት እንደምትነሳ ነገሯቸው። በርካታ ስደተኞች ያለቁበትን የሜዲትራኒያን ባህር ለማቋረጥ ምሽት ምቹ ሰዓት እንደሆነ አስረዷቸው።
ሌላ አማራጭ ስላልነበራቸው ተስማሙ። ስለ ጀልባዋ ሁኔታ ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም- እነሱ የሚያስቡት መዳረሻቸውን ነው። በእንጨት የተሠራ ጀልባ ውስጥ መሳፈራቸውን የነገራቸው አልነበረም፤ እነሱም አላወቁም።
ይሁን እንጂ ለሦስት ሰዓታት ያህል እንደተጓዙ የባህሩ ውሃ ወደ ጀልባዋ መግባት ጀመረ።
"አጠገባችን ባገኘነው እቃ ሁሉ ጀልባ ውስጥ የገባውን ውሃ እየጨለፍን ለማስወጣት ታገልን፤ ቢሆንም ውሃው በፍጥነት ጀልባዋን ሞላት" ይላል ስለነበረው ሁኔታ የሚያስታውሰው በኩረፅዮን።
በዚያ ሰዓት አንድ የንግድ መርከብ እያለፈ ስለነበር ጀልባ ውስጥ ያሉት ሁሉ ለእርዳታ ጮኹ፤ ግን ጆሮ የሰጣቸው አልነበረም።
ከዚያም ጀልባቸው ተሰብራ መስመጥ ጀመረች። ሁሉም እየዘለለ ወደ ባህሩ ገባ። ማንኛቸውም የመንሳፈፊያ ጃኬት እንኳን አለበሱም፤ የሚይዙት የሚጨብጡት ነገር አልነበረም።
በኩረፅዮን እንደሚለው፤ ከመስመጥ ለመዳን መጀመሪያ ላይ የተሰበረ አንድ ጀሪካን በእጁ ጨምድዶ ያዘ። በዚያ ትንሽ ተንሳፎ እንደቆየ ለመንሳፈፍ የሚረዳው ሌላ እንጨት አገኘ። ይህም ሙሉ ሌሊቱን ለማለፍ ረዳው።
ከአደጋው የታደጋቸው አንድ በአጠገባቸው ሲያልፍ የነበረ አሳ አጥማጅ ነው፤ አሳ አጥማጁ ወደ ትሪፖሊ ፖሊስ ጣቢያ አደረሳቸው።
በአፍና በአፍንጫቸው ሲገባ ባደረው ውሃ ምክንያት ሁሉም ትውከት እያጣዳፋቸው ስለነበር አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ተደረገላቸው።
በኩረፅዮን እና በክሪ እስካሁን በሊቢያ ትሪፖሊ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ከጉዳታቸው እያገገሙ ነው።
"የተረፍኩት በፈጣሪ ኃይል ነው፤ እሱ እንድተርፍ ስለፈቀደ ብቻ! ምክንያቱም ዋና እንኳን አልችልም ነበር" ይላል።
በክሪ በበኩሉ የሚረዳቸው ሰው ከማግኘታቸው አስቀድሞ ያነበሩትን ሰባት አሰቃቂና አስጨናቂ ሰዓታት ብዙም ማስታወስ እንደማይችል ይናገራል።
የጀልባ መስመጥ አደጋው ካጋጠማቸው ሁለት ወራት ተቆጥረዋል፤ ነገር ግን ከአደጋው በተዓምር የተረፉት ሁለቱ ጓደኛሞች እስካሁን በጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ። የወደፊት እጣ ፋንታቸው ምን እንደሆነ አያውቁም።
"ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጥሩ እንቅልፍ ተኝቼ አላውቅም። የጓደኞቼ፣ ጀልባው ላይ ተሳፍረው የነበሩት ሰዎች ፊት በሕልሜ ይመጣብኛል" ይላል በኩረፅዮን።
"ስለ ሕይወቴም አብዝቼ እጨነቃለሁ። ምን እንደሚገጥመኝ አላውቅም። ምን ማድረግ እንዳለብንም አናውቅም " ሲል ጭንቀቱን ያስረዳል።
ባሳለፍነው ሃምሌ ወር ላይ 300 የሚሆኑ ስደተኞችን ጭና ስትጓዝ የነበረችው ይህች ጀልባ ሰጥማ በትንሹ 115 የሚሆኑት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።