የሶማሊያ ባለስልጣናት ከአልሸባብ ጋር በተያያዘ የጎሳ መሪዎችን አስጠነቀቁ

የሶማሊያ ግዛት በሆነችው ጁባላንድ የአስተዳደር ክልል ውስጥ ታጣቂው እስላማዊ ቡድን አልሸባብ የሚያወጣቸውን መመሪያዎች ተግባራዊ በሚያደርጉ የጎሳ መሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።

አስተዳደሩ ባወጣው ማስጠንቀቂያ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የጎሳ መሪዎች አልሸባብ ይካሄዳል የተባለው የምርጫ ሂደትን እንዲያወግዙና ለታጣቂ ቡድኑ ታማኝነታቸውን እንዲገልጹ ያቀረበውን ጥሪ ተከትለው የተባለውን ድርጊት ከፈጸሙ አስፈላጊውን የቅጣት እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

አልሸባብ በቅርቡ ባወጣው ትዕዛዝ የፓርላማ አባላትን በመምረጥ ሂደት ውስጥ የተሳተፉ የጎሳ መሪዎች ድርጊታቸውን በማውገዝ "ንሰሐ" እንዲገቡ አለዚያም ሞት እንደሚጠብቃቸው አስጠንቅቆ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጎሳ መሪዎች እስላማዊው ቡድን ሊወስድ በሚችለው እርምጃ ለሕይወታቸው በመስጋት ቡድኑ ላቀረበው ጥሪ ምላሽ ሰጥተዋል።.

በዚህም የጁባላንድ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ ለአልሸባብ ጥሪ ተገዢ በመሆን ምላሽ የሚሰጡ የጎሳ መሪዎች የስድስት ወራት እስራትና የሽምግልና ቦታቸውን እንዲያጡ ከመደረጉም በላይ እያንዳንዳቸው ሁለት መትረየሶችን በቅጣት መልክ ለአስተዳደሩ እንዲሰጡ ይገደዳሉ።

አልሸባብ በበኩሉ በምርጫው ሂደት የተሳተፉ የጎሳ መሪዎች "የንሰሐ ቅጣት" በሚል እያንዳንዳቸው አንድ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ከአራት ካርታ ጥይቶች ጋር እንዲያስረክቡ አዞ ነበር።

ትናንት ማክሰኞ በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ በምትገኘው ቡላይ ፉላይ መንደርና በጁባላንድ አንድ መቶ የሚደርሱ የጎሳ መሪዎች "ንስሐ" በመግባታቸው ይቅርታ አድርጎላቸዋል ተብሏል።

ከጁባላንድ በተጨማሪ ጋልሙዱግ በተባለውና በሌሎች የደቡብ ምዕራብ የሶማሊያ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ አስተዳዳሪዎች ከአልሻባብ ጋር ግንኙነት የሚፈጽሙ የጎሳ መሪዎችን አስጠንቅቀዋል።

አልሻባብ በሶማሊያ ውስጥ እስላማዊ አስተዳደር ለመመስረት የሚፈልግ ቡድን ሲሆን አሁን ያለው የሶማሊያ መንግሥትን እውቅና በመንፈግ በኃይል ለማስወገድ የተለያዩ ጥቃቶችን እየፈጸመ የሚገኝ ቡድን ነው።