ቆዳን ለማንጣት የሚከፈል ዋጋ፡ የሴቶች የቆዳ ክሬሞች የደቀኑት አደጋ

በርካታ ሴቶች የፊትን ቆዳ የሚያፈኩ ክሬሞችን ይጠቀማሉ። እነዚህ ክሬሞችም ሆኑ ቅባቶች ሕጋዊና ጤንነታቸው የተጠበቁ ካልሆኑ በቆዳና በአጠቃላይ ጤና ላይ ጠንቅን እንደሚያስከትሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በተለይ በአፍሪካና በእስያ አህጉራት የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በርካታ ሴቶች የቆዳቸውን ገጽታ ለማፍካት ብዙ ርቀት ተጉዘው ጉዳትን የሚጋብዙ ነገሮችን ይጠቀማሉ።

በዓለም ዙሪያ ያሉ ቆዳን የሚያፈኩ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች በፈረንጆቹ 2017 ላይ 4.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢን ያገኙ ሲሆን ይህ አሃዝም ከሃያ ዓመታት በኋላ በእጥፍ እንደሚያድግ ይጠበቃል። ለእነዚህ ምርቶች ከፍተኛው ፍላጎት ያለው ደግሞ በአፍሪካና በእስያ ባሉና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሰዎች ዘንድ ነው።

እነዚህ ምርቶች ሳሙናን፣ ክሬሞችን፣ እንዲሁም በሰውነት ውስጥ የቆዳ ቀለምን የሚቆጣጠሩ የተፈጥሯዊ ንጥረ ነገሮች መመንጨትን ለማዘግየት ያስችላሉ የተባሉ የሚዋጡ እንክብሎችንና በመርፌ የሚደሰጡ ምርቶችንም ያካትታል።

የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ 10 ሴቶች 4ቱ ቆዳን የሚያፈኩ ምርቶችን ይጠቀማሉ።

በዚህ በኩል ናይጄሪያ ከሁሉም ሃገራት ቀዳሚ ስትሆን 77 በመቶ የሚሆኑ የሀገሪቱ ሴቶች ቆዳን የሚያፈኩ ምርቶችን ይጠቀማሉ። ቶጎ በ59 በመቶ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ በ35 በመቶ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል።

በአህጉረ እስያ ውስጥ ደግሞ ከህንድ ሴቶች 61 በመቶዎቹ፤ ከቻይና ሴቶች ደግሞ 40 በመቶዎቹ ምርቶቹን በስፋት ይጠቀማሉ።

ዓለም አቀፋዊ ፈተና

እነዚህ ምርቶችን በተመለከተ የሰዎች ፍላጎት በጨመረ ቁጥር አብሮት ያለው ተግዳሮትም ከፍ ይላል።

ጋናዊያን ሴቶች በማህጸናቸው ውስጥ ያለን ጽንስ ቆዳ ያፈካዋል በሚል ተስፋ ሲወስዱት የነበረውን እንክብል፤ ባለፈው ዓመት የጋና ባለስልጣናት እንክብሉ በውስጡ በያዘው ንጥረ ነገር ምክንያት ነፍሰጡር ሴቶች እንዳይጠቀሙ ማስጠንቀቂያ አውጥተው ነበር።

ቆዳን ያፈካሉ ከሚባሉ ምርቶች አንጻር ጠንካራ ሕግ ካላቸው ጥቂት የአፍሪካ ሃገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ አንዷ ናት። ጋምቢያ፣ ኮትዲቯርና በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ደግሞ ሩዋንዳ ሜላኒን የተባለውን በሰውነታችን ውስጥ የሚመረት ንጥረ ነገር እንዲቀንስ የሚያደርግ ይዘት ያላቸውና በቆዳ ላይ ዘላቂ ጉዳትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ቆዳን ሚያፈኩ ምርቶች ወደ ሃገራቸው እንዳይገቡ ከልክለዋል።

ሜላኒን የተባለው ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገር ቡናማ ወይም ጥቁር ሲሆን ለቆዳችን የሚሆነውን ቀለም ያመነጫል።

የባለሙያዎች ሚና

የብሪታኒያ የቆዳ ጤና ተቋም እንዳለው ለቆዳ ቀለም ተብለው ጥቅም ላይ ከሚውሉት ምርቶች ውስጥ በባለሙያ ትዕዛዝና ክትትል የሚሰጡ እንዳሉና አንዳንድ የቆዳ ማፍኪያ ምርቶችም እንዲሁ የሚወሰዱ እንዳልሆነ አመልክተዋል።

የተቋሙ ቃል አቀባይ የሆኑት አንተን አሌክሳንድሮፍ እንደሚሉት "አንዳንዶቹ የቆዳ መፍኪያ ምርቶች ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን በቆዳ ሐኪም መታዘዝና የቅርብ ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል። ካልሆነ ግን ውጤታቸው አደገኛ ነው።"

የብሪታኒያ የቆዳ ጤና ተቋም እንደሚለው ደግሞ የቆዳ ቀለምን በማፍካት በኩል እውቅና የተሰጠውና አስተማማኝ የሆነ ዘዴ የለም።

ያለሃኪም ትዕዛዝ ጥቅም ላይ የሚውሉ ክሬሞች ጠቃሚ መሆናቸውን የሚያመለክት ነገር የለም። ምናልባትም ከሚጠበቀው ተቃራኒ ውጤትን ሊያስከትሉ ይችላሉ፤ የሚሉት ቃል አቀባዩ "ቆዳን ተፈጥሯዊ ከሆነው ውጪ ሊያነጡ ወይም ሊያጠቁሩ ከመቻላቸው በተጨማሪ የቆዳን ተፈጥሯዊ ውበትን ሊያጠፉ ይችላሉ" በማለት ያስጠነቅቃሉ።

የጎንዮሽ ጉዳት

ከባለሙያ ትዕዛዝና የቅርብ ክትትል ውጪ ቆዳን የሚያፈኩ ምርቶችን የሚጠቀሙ ሰዎች የሚከተሉትን የመሳሰሉ ከበድ ያሉ የጎንዮሽ ውጤቶች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ።

የቆዳ መንደብደብና እብጠት

የማቃጠልና የመቆጥቆጥ ስሜት

ማሳከክና የቆዳ መሰነጣጠቅ

(ምንጭ፡ ኤንኤችኤስ ዩኬ)

የሃገራት አቋም

ቆዳን በማቅላት በኩል ፈጣን ውጤትን እንደሚያስገኙ የሚነገርላቸው አንዳንድ ምርቶች ደግሞ ጎጂ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን የያዙ ናቸው።

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በውስጣቸው የሜርኩሪ ንጥረ ነገርን የያዙ ቆዳን የሚያፈኩ ምርቶች ለጤና በጣም አደገኛ ናቸው። ጨምሮም ሜርኩሪ በውስጣቸው የሚገኙ ምርቶችን በቻይና፣ በዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ በሌባኖስ፣ በሜክሲኮ፣ በፓኪስታን፣ በፊሊፒንስ፣ በታይላንድና በአሜሪካ ውስጥ እንደሚመረቱ ጠቁሟል።

የአውሮፓ ሕብረትና በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ሜርኩሪን በውስጣቸው የያዙ የቆዳ መንከባከቢያ ምርቶች ላይ እገዳ የጣሉ ሲሆን፤ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ፊሊፒንስና ሌሎች ጥቂት ሃገራት ደግሞ በዝቅተኛ መጠን እንዲኖር ይፈቅዳሉ።

ሜርኩሪ

ሜርኩሪ የተለያዩ የጤና ችግሮችን የሚያስከትል "መርዝ ነው" ይላሉ ቃል አቀባዩ አሌክሳንድሮፍ፤ ቆዳን በሚያፈኩ ክሬሞችና ሳሙናዎች ውስጥ በሚገኝ ሜርኩሪ ሳቢያ ከሚከሰቱ ተጓዳኝ ችግሮች መካከል

  • የኩላሊት መጎዳት
  • የቆዳ መንደብደብ፣ የቆዳ ቀለም መዛባትና ጠባሳ
  • ባክቴሪያና ሌሎች ኢንፌክሽኖችን የመከላከል አቅም መቀነስ
  • ጭንቀት፣ ድብርት ወይም ሌላ የአእምሮ ችግር

(ምንጭ: የዓለም ጤና ድርጅት)

ጥንቃቄ

በፊንበርግ የህክምና ትምህርት ቤት መምህርና የውበት መጠበቂያ ምርቶች በሚያስከትሉት አሉታዊ ውጤት ላይ ምርምር ያደረጉት አሜሪካዊው የቆዳ ሃኪም የሆኑት ዶክተር ሹይ ዡ እንደሚሉት "አንዳንድ የቆዳ ክሬሞችን በአግባቡ ካልተጠቀምንባቸው በውስጣቸው የሚይዟቸው ንጥረ ነገሮች ጉዳትን ያስከትላሉ።"

ገበያው ተመሳስለው በተሰሩ ምርቶች የተጥለቀለቀ በመሆኑ ሃሰተኞቹን ከትክክለኛው ለመለየት አስቸጋሪ ነው። አስመስለው የሚሰሩትን፣ የሚያጓጉዙበትንና የሚሸጡበትን መንገድ መለየት ለትክክለኞቹ አምራቾች አዳጋች እንደሆነም ይነገራል።

ለዚህ ደግሞ ጠንካራ የመቆጣጠሪያ ደረጃዎችን ማዘጋጀት አደገኛ ምርቶችን ወደ ገበያ እንዳይገቡ ለማድረግ እንደሚያስችል ዶክተሩ ይመክራሉ። ጨምረውም ከበድ ያለ ውጤት ያላቸውን ምርቶች ተጠቃሚዎች ሲገዙ የባለሙያ ምክርና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

የተዛባ አመለካከት

በተለያዩ ማህበረሰቦች ባህልና ቋንቋ ውስጥ ነጭ ቀለም በአብዛኛው ከሰላም፣ ከውበት፣ ከአዋቂነት ጋር የተዛመደ ትርጉም ሲሰጠው ጥቁር ደግሞ ከሞት፣ ከአደጋ፣ ከመጥፎ ገጽታና ስሜት ጋር ተመሳሳይ ተደርጎ ይወሰዳል።

ከውበት አንጻር ዘወትር እንደሚባለው ዋነኛው ውበት ውስጣዊ ነው፤ ነገር ግን በቆዳ ቀለም አንጻር ያለው የተሳሳተ አመለካከለት እጅጉን ስር የሰደደ ነው። ይህ ደግሞ በርካቶች የቆዳ ቀለማቸውን 'ለማስተካከል' ጤንነታቸውን ለጉዳት እስከሚዳርግ እርምጃ ድረስ እንዲሄዱ እየገፋቸው ነው።

አመለካከትን መለወጥ

የመዝናኛው ኢንደስትሪም የተወሰነ አይነት የሰውነት ቅርጽና የቆዳ ቀለምን ተቀባይነት እንዲያገኝ በመስራቱ ከመወቀስ አልፎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴቶች ላይ በጎ ያልሆነ ስሜትን ፈጥሯል።

የቁንጅና ውድድሮችና ማስታወቂያዎች ላይ የፈካ የቆዳ ቀለም ከፍ ያለ ትኩረት የሚሰጣቸው በመሆኑ በርካቶች ቆዳን የሚያፈኩ ምርቶችን አንዲጠቀሙ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጽእኖ ሲፈጥሩ እንደቆዩ ይገመታል።

ይህንንም አመለካከት ለመለወጥ የተለያዩ የማህበረሰብ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ከእነዚህም መካከል ህንዳዊያን ሴቶች ያላቸውን የቆዳ ቀለም ተቀብለው ለማንጣት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲተዉ "ጥቁር ውብ ነው" በሚል የተጀመረው ዘመቻ አንዱ ነው። ፓኪስታን ውስጥም "ቆንጆ ለመባል የነጣ ቆዳ አያስፈልግም" የሚል እንቅስቃሴ አለ።

በአሜሪካም በሶማሊያ ስደተኞች ላይ ትኩረት በማድረግ ቆዳን የሚያፈኩ ተግባራትንና ለተለያዩ ጎጂ ኬሚካሎች ያለውን ተጋላጭነት ለማስወገድ ተመሳሳይ በአንድ ቡድን አማካይነት ጥረት እየተደረገ ነው።

ህንድ ውስጥ ከእምነት አንጻር የሚወከሉ የአማልክት ምስሎች ነጭ የቆዳ ቀለም ስላላቸው ይህንን ለመቀየር ጥቁር ገጽታ እንዲኖራቸው በማድረግ "ጥቁር መለኮታዊ ነው" የሚል እንቅስቃሴም ተጀምሯል።