ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያና የኤርትራ አዲስ ግንኙነት በአንደኛ ዓመት
ልክ የዛሬ አንድ ዓመት የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ ሰኔ 13 የሚዘከረው የሰማዕታት ቀንን ምክንያት በማድረግ ባደረጉት ንግግር መንግሥታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበው የሰላም ጥሪ እንደተቀበለው እና ከፍተኛ የመንግስት ልኡካን ወደ አዲስ አበባ እንደሚልክ ተናግረው ነበር።
እነሆ ያች ቀን አንድ ዓመት ሞላት። ባለፉት 12 ወራት ሁለቱ ሃገራት የት ደረሱ? ጎልተው ከሚጠቀሱት ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ጥቂቶቹን ልናስታውሳቹ ወደድን።
• ግንቦት 29/2010 - የመከረው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦችን ሰላም ለማስጠበቅ የአልጀርስ ስምምነት ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታወቀ፤
• ሰኔ ወር መገባደጃ ገደማ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዑስማን ሳልሕ እና የፕሬዝደንት ኢሳያስ አማካሪ የማነ ገብረአብ የመሩት ከፍተኛ የመንግስት ልዑክ አዲስ አበባ ገባ፤
• ሐምሌ 1/2010 - የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ፤ ከ20 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው የሆነውን ታሪካዊ ይፋ የስራ ጉብኝት ለማድረግ አስመራ ገቡ፤
• ሐምሌ 14/2010 - በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥሪ መሠረት የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ ደረሱ፤
• ሐምሌ 2/2010 - ሁለቱ ሃገራት አስመራ ላይ በደረሱት 'የሰላምና የወዳጅነት አዋጅ' መሠረት ለ20 ዓመታት ያክል ተቋርጦ የነበረውን የአየር በረራ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካይነት እንደ አዲስ ጀመረ፤
• የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ሁለቱ ሃገራት በቀጠናው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ላደረጉት አስተዋጽኦ "ኒሻን ዛይድ" ለጠ/ሚር አብይ እና ለፕሬዝደንት ኢሳያስ አጠለቀች፤
ነሐሴ
• ነሐሴ 30/2010 - ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝደንት መሐመድ ፎርማጆ አስመራ ላይ ተገናኝተው የሃገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክር ያሉትን የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈራረሙ፤
መስከረም
• መስከረም 1/2011 - ኤርትራንና ኢትዮጵያ ከሚያገናኙት የምድር ትራንስፖርት መንገዶች ሁለት ማለትም ደባይሲማ-ቡሬ እና ሰርሐ-ዛላምበሳ ከ20 ዓመታት በኋላ ተከፈቱ። ይህንን በሥፋራው በመገኘት ያበሰሩት ደግሞ የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ነበሩ፤
• የድንበሩን መከፈት ተከትሎ 'የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዝምድና ሰላማዊ መልክ ለማስያዝ ባደረጉት አስተዋጽኦ' በሚል የሳዑዲ አራቢያ መንግሥት "የንጉስ አብደልአዚዝ ኒሻን" ሽልማትን አበረከተላቸው፤
• መስከረም 18/2011 - ከኢትዮ-ኤርትራ እርቅ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤርትራ የሚኒስትሮች ካቢኔ ተሰበሰበ። ካቢኔው በቀጠናው ስለሚታዩ ስትራቴጂካዊ ትብብሮች ሰፊ ውይይት አካሄደ፤
ታኅሣሥ
• መስከረም ወር ላይ የተከፈተው የዛላምበሳ-ሰርሓ ድንበር ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ ጉዳይ ከፌደራል መንግስት ፍቃድ ለሌላቸው ተጓዦች ዝግ እንደሆነ ተነገረ። ቀጥሎ ታኅሣሥ 27 የራማ-ክሳድ-ዒቃ መስመር በተመሳሳይ ምክንያት ተዘጋ፤
ጥር
• ጥር 13/2011 - ጣሊያን ከባጽዕ ወደ አዲስ አባባ የሚገነባው የባቡር መስመርን ለማገዝ ፍቃደኛ ነኝ አለች፤ በወቅቱ ጣልያን የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ነበሩ ይህን ያበሰሩት፤
ግንቦት
• ግንቦት /2011 - የኤርትራ የነጻነት ቀን አከባበር ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝደንት ኢሳያስ 'ለለውጥ ጥድፊያ አያስፈልግም' ሲሉ ተደመጡ፤
ሰኔ
• ሰኔ 12/2011 - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከኤርትራ ልዑክ ጋር ተገናኙ። ልዑኩን እየመሩ የመጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኡስማን ሳልሕና የፕሬዝደንቱ አማካሪ አቶ የማነ ገብረአብ ነናቸው።
ባለፉት 12 ወራት ኢትዮጵያ ሆነ ኤርትራ በውስጥ ሃገር ፖለቲካ የተረጋጋ የሚባል ጊዜ አልነበራቸውም፤ ስኬታማ ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉ ሥራዎች መሠረታቸው ሳይዘነጋ።
ነገር ግን ሁለቱ ሃገራት ብዙ የተባለለትን የሰላም ስምምነት በአግባቡ አልተጠቀሙበትም ሲሉ የሚተቹ በርካቶች ናቸው፤ ከዳያስፖራው ማሕበረሰብ ጫና የበረታባቸው ፕሬዝደንት ኢሳያስ 'ለውጥ ጥድፊያ አይወድም' ቢሉም ቅሉ።