በጦርነት የተጎሳቆሉ ስደተኞች መዳረሻቸው የት ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መኖሪያ ሃገራቸው በጦርነትና በግጭት ሲናጡ፤ ግለሰቦች መንግሥታት ሲያሳድዷቸውና መተንፈሻ ሲያጡ ህይወታቸውን ለማቆየት ወደየት ይሄዱ ይሆን?
መረጃዎች እንደሚያሳዩት የትኛውም ሃገር ላይ 80% የሚሆኑት ነዋሪዎች እዛው በችግር እየተቆራመቱ የሚቆዩ ሲሆን፤ አማራጭ አጥተው ከሚሰደዱት ደግሞ 80%ቱ ጎረቤት ሃገራት ይቆያሉ።
የስደተኞችን ቀን በምንዘክርበት በዛሬው እለት በጎርጎሳውያኑ ያለፈው አመት የስደተኞች መሸጋገሪያ የሆኑ ስድስት ሃገራትን እንመለከታለን።
ቱርክ
ከየትኛውም አገር በበለጠ ቱርክ ስደተኞችን ትቀበላለች። በተለይም ከስምንት አመታት በፊት በተነሳው የጎረቤቷ ሶሪያ የርስበርስ ብጥብጥን ተከትሎ የስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።
ከዚህም በተጫማሪ ራቅ ካለችው አፍጋኒስታንም ብዙ ስደተኞች የሚተሙ ሲሆን፤ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጂያ ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) መረጃ እንደሚያሳየው ከአለም ስደተኞች ውስጥ 1/5ኛውን ስደተኞች የምትቀበለው ቱርክ ናት።
ፔሩ
ፔሩ ስደተኞችን በመቀበል ሁለተኛ ስትሆን ይህም የጎረቤቷ ቬንዙዌላ የኢኮኖሚ ቀውስን ተከትሎ ነው።
በጎርጎሳውያኑ 2015 ጀምሮ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች ወደ ጎረቤት ኃገራት እንደተሰደዱ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
ይህንንም ተከትሎ የስደተኞችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ፔሩ ጠበቅ ያለ አዲስ ህግ አስተዋውቃለች።
ሱዳን
አብዛኛውን ወደ ሱዳን የሚገቡት ስደተኞች በርስ በርስ ጦርነት ከምትበጣበጠው ደቡብ ሱዳን ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ከመካከለኛው ምስራቅ ካሉት አገራት ውጭ የሶሪያ ስደተኞችን በመቀበል ከአለም ሶስተኛ ናት።
ነገር ግን ሱዳን የራሷ 724ሺ 800 ስደተኞች በባለፈው አመት አገሪቷን ለቀው ወጥተዋል።
ኡጋንዳ
ኡጋንዳ እርስ በርስ ግጭት እየተናጡ ካሉት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎና ደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ተቀብላለች።
ከኮንጎ የተቀበለቻቸው ስደተኞች ወደ 120ሺ የሚጠጉ ሲሆን፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ህፃናት በመቀበልም ከአለም አንደኛ ናት።
በባለፈው አመትም 83 ሺ 600 ስደተኞች ወደ ደቡብ ሱዳን ተመልሰዋል።
አሜሪካ
ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ስደተኞችን የመቀበል አዝማሚያ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ቢሆንም፤ አሁንም በአለም የጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር አለምን ትመራለች።
ስደተኞቹ ከ166 አገራት የተውጣጡ ቢሆንም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ግን ከመካከለኛው አሜሪካ አራት ሃገራት በተለይም ከሜክሲኮ ነው።
ከቀደሙት ሃገራት ጋር ሲወዳደር የጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሽቆለቆለ እየተነገረም ነው።
ጀርመን
ጀርመን ከሚሊዮን ለሚበልጡ ስደተኞች ቤት ስትሆን፤ 532ሺዎቹ የመጡት በጦርነት እየወደመች ካለችው ሶሪያ ነው።
ከሶሪያ በተጨማሪ ከኢራቅም የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር ከፍተኛ ነው።
በአዲስ ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር ከአለም ሶስተኛ ብትሆንም ከ2016 በኋላ ቁጥሩ ያሽቆለቆለ ሲሆን፤ በባለፈው አመት ብቻ በ14% እንደወረደ ተገልጿል።
ሁሉም መረጃዎች የተገኙት ከተባበበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ነው












