ኒፕሲ ሐስልን እንደገደለ የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, David Crotty
በአባቱ ኤርትራዊ የሆነው እና የግራሚ እጩው ራፐር ኤርምያስ አስገዶም (ኒፕሲ ሐስልን) ሳይገድል አይቀርም ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብ በሎስ አንጀለስ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ባለስልጣናት አስታወቁ።
የ29 ዓመቱ ዓመቱ ኤሪክ ሆልደር የሚባለው ተጠርጣሪ ግድያው ከተፈጸመበት ቦታ ቆሞ ሲጠብቀው በነበረው መኪና ከአካባቢው ከተሰወረ በኋላ በቁጥጥር እስከሚውልበት ሰዓት ድረስ ተደብቆ እንደቆየ የሎስ አንጀለስ ፖሊስ አሳታውቋል።
ኒፕሲ ወይም ኤርምያስ ባሳለፍነው እሁድ ከልብስ መሸጫው አቅራቢያ በጥይት ተመትቶ መገደሉ ይታወሳል።
መርማሪ ፖሊሶች የግድያው መንስዔ በገዳይ እና በሟች መካከል የነበረ ''ግላዊ ጉዳይ'' እንደሆነ እምነት አድሮባቸዋል።
የሎስ አንጀለስ ፖሊስ አዛዥ ማይክል ሞር ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ተኩስ ከመከፍቱ በፊት ተጠርጣሪ እና ራፐሩ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲጨቃጨቁ ነበር።
የፖሊስ አዛዡ እንደሚሉት ከሆነ ከጭቅጭቁ በኋላ ተጠርጣሪው ስፍራውን ለቅቆ ከሄደ በኋላ የጦር መሳሪያ ይዞ እንደተመለሰ እና ተኩስ እንደከፈተ ተናግረዋል።
ከአካባቢው የተገኘ ተንቀሳቃሽ ምስል ጥቁር ቲ-ሸርት የለበሰ ሰው ሶስት ጊዜ ከተኮሰ በኋላ በመኪና ከአካባቢው ሲሰወር ያሳያል። በተከፈተው ተኩስ ሁለት ሌሎች ሰዎች ጉዳት አጋጥሟቸዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ

ትናንት ለኒፕሲ ጸሎት እየተደረገለት ሳለ አንድ ግለሰብ የጦር መሳሪያ በማውጣት ቁጣውን ሲያሰማ ሌላው መሳሪያውን ሊያስጥለው ሲሞክር በተፈጠረ ግርግር እና መረጋገጥ 19 ሰዎች ለጉዳት ተዳርገዋል። ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ ሁለቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የራፐሩ 'ቪክተሪ ላፕ'' አልበም ለዘንድሮው የግራሚ ሽልማት እጩ ነበር።
የራፐሩ ትክክለኛ ስም ኤርሚያስ ዴቪድሰን አሰገዶም ሲሆን እድገቱ ደቡባዊ ሎስ አንጀለስ ውስጥ ሆኖ በአፍላ እድሜው 'ሮሊን ሲክስቲስ' የሚሰኝ የውንብድና ቡድን አባል ነበር።
ከዚያም ከውንብድና ቡድኖች በማራቅ በተለያዩ የማህበረሰብ አቀፍ ስራዎችና በኪነጥበብ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ይታወቃል።
"ያደኩት በውንብድና ቡድኖች ውስጥ ነው" ሲል ለሎስ አንጀለስ ታይምስ በአንድ ወቅት ቃለ መጠይቅ ሰጥቶ ነበር አክሎም "... ሞት፣ ግድያ የየዕለት ትዕይንቶቻችን ነበሩ። በጦርነት ቀጠና ውስጥ እንደመኖር ነው፤ ከዚህ መንደር ሰዎች ሲሞቱ ከቁብ አይቆጠርም ነበር" ብሏል።
ኤርሚያስ ከመገደሉ በፊት በነበረ አንድ እሁድ "አምርሮ የሚጠላህ ሲኖር መባረክ ነው" በማለት በቲውተር ገፁ ላይ አስፍሯል።












