ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ትራምፕ ከሩስያ ጋር አልዶለቱም"
ላለፉት ሁለት ዓመታት ጥልቅና ሰፊ ምርመራ ሲካሄድባቸው ነበር፤ ዶናልድ ትራምፕ ላይ። ምርመራው ሂላሪን ያሸነፉት ከሩስያ ጋር ዶልተው ነው ከሚል ጥርጣሬ የተጀመረ ነው። ሩስያ በእርግጥ በ2016ቱ የአሜሪካ ምርጫ እጇን አስገብታ ነበር? ብዙዎች የዚህን ጥያቄ ምላሽ በጉጉት ሲጠብቁ ነበር።
"የሙለር ምርመራ" ተብሎ የሚጠራው ይህ ሂደት የዶናልድ ትራምፕን የቅርብ ረዳቶች ሳይቀር ዘብጥያ እንዲወርዱ ያደረገ ነበር። ግማሾቹ የሕግ ሂደትን በማደናቀፍ፣ ከፊሎቹ በምርመራ ወቅት ዋሽታችኋል፣ ሐቅ መናገር ተናንቋችኋል በሚል እስር ተበይኖባቸው ነበር።
በመጨረሻም ይህ ምርመራ ውጤቱ ትናንት እሁድ ለኮንግረስ ቀርቧል።
የትራምፕ ምርጫ ዘመቻ ከሩስያ ጋር ምንም ዓይነት መመሳጠር አልነበረበትም ብሏል፣ ሪፖርቱ።
ያም ሆኖ ሪፖርቱ ትራምፕ የሕግ ሂደትን ስለ አለማደናቀፋቸው ወይም ከወንጀል ሙሉ በሙሉ ነፃ ስለመሆን አለመሆናቸው ድምዳሜን አይሰጥም።
ሪፖርቱ ለኮንግረሱ የቀረበው በልዩ አቃቢ ሕግ ዊሊያም ባር ፍሬ ሐሳቡ ከተጠናቀረ በኋላ ነበር።
ዶናልድ ትራምፕ የሪፖርቱን መውጣት ተከትሎ "መመሳጠርም ሕግ ማደናቀፍም ብሎ ነገር የለም" የሚል መልዕክት በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ጽፈዋል።
ትራምፕ እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "በሌለ ነገር ይህን ሁሉ ጊዜ ማጥፋት ያሳፍራል" ብለው ነበር።