አልጄሪያዊው ፕሬዚዳንት አብደላዚዝ ቡተፍሊካ ለአምስተኛ ጊዜ እንደማይወዳደሩ አስታወቁ

የአልጄሪያው ፕሬዝዳንት አብደላዚዝ ቡተፍሊካ በቀጣዩ ምርጫ እንደማይሳተፉ አስታወቁ።

የ82 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ለአምስተኛ ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸው ነበር።

ለ20 ዓመታት በስልጣን የቆዩት ፕሬዝዳንቱ ከባድ የጤና እክል ካጋጠማቸው ሰነባብቷል።

የምርጫው ጊዜም ላልተወሰነ ጊዜ የተራዘመ ሲሆን ከመንግስታቸው የወጣ መግለጫ እንደሚያትተው በቅርቡ የካቢኔ ሹም ሽር እንደሚደረግ ነው።

መግለጫው ፕሬዚዳንቱ ከምርጫው በፊት ስልጣን ይለቁ ይሆን ወይ ለሚለው ዝርዝር መረጃ የለውም።

በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ኡሃያ ስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ኑረዲን ቤዱ እንደተኳቸው ተዘግቧል።

"ለአምስተኛ ጊዜ አልወዳደርም " የሚለው መግለጫቸው አክሎም " ከጤናዬና ከእድሜዬ አንፃር እንደማልወዳደር ሳይታለም የተፈታ ነው። በመጨረሻም ለአልጀሪያውያን ማድረግ የምፈልገው ለአዲሲቷ ለሚፈጥሯት አገር መሰረትን መጣል ነው። "

እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ2014 በሀገሪቱ በተካሄደው ምርጫ አሸንፈው በ1999 የተረከቡትን ስልጣን ሲያስቀጥሉ በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብለው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከዚያን ቀን ጀምሮ ግን የውሃ ሽታ ሆነዋል። ሀገሪቱም በማይታይ ፕሬዚዳንት መመራት ከጀመረች እነሆ ስድስት አመት ሆናት።

በመጪው ምርጫ እሳተፋለሁ ማለታቸው ከፍተኛ ተቃውሞን አስነስቶ የነበረ ሲሆን፤ አንድ ሺ የሚሆኑ ዳኞችም ቀጣዩ ምርጫ ላይ ላለመሳተፍ አድማ ማስነሳታቸውና ሰራዊቱም ከተቃዋሚዎቹ ጎን መሆን በምርጫው እንዳይሳተፉ እንደገፋቸው ተዘግቧል።