በታሪክ ከፍተኛ መጠን ያለው አደገኛ ዕፅ በአሜሪካ-ሜክሲኮ ድንበር ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ገቢዎች እና ደንበር ጥበቃ ባለስልጣን በታሪኩ ከፍተኛ መጠን ያለውን አደጋኛ ዕፅ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ሰራተኞች እንዳስታወቁት 114 ኪሎ ግራም የሚመዝን 'ፌንታኒል' እና 180 ኪሎ ግራም የሚመዝን 'ሜታአፌታሚን' የተሰኙ አደገኛ እፆችን በጭነት መኪና በሜክሲኮ-አሜሪካ ድንበር ላይ በቁጥጥር ሥር አውለናል ብለዋል።
የአሪዞና ግዛትን እና ሜክሲኮን የሚያገናኘው የደንበር ጥበቃ ኃላፊ የሆኑት ማይክል ሃምፕሪስ እፆቹን የስንዴ ዱቄት በማስመሰል ድንበር ለማሻገር ተሞክሯል ብለዋል።
ሜክሲካዊው የጭንት መኪና አሽከርካሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉን እና ክስ እንደተመሰረተበትም ተነግሯል።
የደንበር ጥበቃ ኃላፊው እንደሚሉት ከሆነ በቁጥጥር ሥር የዋለው 114 ኪሎ ግራም የሚመዝነው 'ፌንታኒል' የተሰኘው ዕፅ ብቻ ወደ አሜሪካ መግባት ቢችል ኖሮ በጥቁር ገብያው ላይ 3.5 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያወጣ ነበር።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ 'ፌንታኒል' የተሰኘው በጣም በትንሹ እንኳ ቢወሰድ ለሞት ሊዳርግ ይችላል።
የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል አህዞች እንደሚያሳዩት እአአ 2016 ብቻ 18ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ይህን ዕፅ ከመጠን በላይ ወስደው ህይወታቸው አልፏል።













