ሃዩንዳይ የሚራመድ መኪና አምርቷል

ሃዩንዳይ የተባለው የመኪና አምራች ድርጅት ከባድ ተፈጥሮአዊ መልክአምድር ሲያጋጥመው እግሮቹን ዘርግቶ መራመድ የሚችል 'ኤሌቬት' የተሰኘ መኪና አምርቶ ለሙከራ አቅርቧል።

መኪናው በተገጠሙለት አራት እግሮች በሰአት አምስት ኪሎሜትር መጓዝ የሚችል ሲሆን 1.5 ሜትር ከፍታ መውጣትና 1.5 ሜትር ደግሞ ወደላይ መዝለል እንደሚችል ተገልጿል።

መኪናው የተፈጥሮ አደጋዎች ሲያጋጥሙ የእርዳታ ስራ ለመስራት እጅግ ጠቃሚ እንደሚሆን አምናለሁ ብሏል አምራቹ ሃዩንዳይ።

የመኪናውን ጽንሰ ሃሳብ ማሳደግና የግንባታ ስራውን ማጠናቀቅ ሶስት ዓመታትን የፈጀ ሲሆን በአሜሪካዋ ላስ ቬጋስ ከተማ ለእይታ ቀርቧል።

''ከባድ አውሎ ነፋስ አልያም የመሬት መንቀጥቀጥ ሲያጋጥም፤ ለሙከራ የተሰራው አዲስ መኪና እጅግ ከፍተኛ ግልጋሎት ይሰጣል። ከፈራረሱ ህንጻዎች ስር የተጎዱ ሰዎችን ለማውጣትም ወሳኝ ነው'' ብለዋል የሃዩንዳይ ምክትል ፕሬዝዳንት ጆን ሱህ።

'ኤሌቬት' ማንኛውም አይነት መልክአምድርና የአደጋ ቦታዎች በቀላሉ መውጣት ስለሚችል ጎርፍና መሰል አደጋዎች ሲከሰቱም ጥቅም ላይ መዋል ይችላል ብለዋል ምክትል ፕሬዝዳንቱ።

መኪናው ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ መራመድ የማይችሉና በዊልቼር ለሚንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኞችም እርዳታ መስጠት የሚችል ሲሆን ያሉበት ድረስ በመሄድ ወደ መኪናው እንዲገቡ ማድረግ ይችላል ተብሏል።