ግብጽ በመካከለኛው ምስራቅ ትልቁን ካቴድራል ከፈተች

የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በመካከለኛው ምስስራቅ ትልቁ የተባለውንና 8000 ሰዎች በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችለው የኮፕቲክ ካቴድራል በዋና ከተማዋ ካይሮ መርቀው ከፍተዋል።

በአዲስ መልክ የተገነባው ህንጻ በገና በአል ዋዜማ እሁድ ዕለት ለምእመናን ክፍት የሆነ ሲሆን፤ በከፍተኛ ጥበቃ ስርም ነበር ተብሏል።

ቅዳሜ ዕለት ናስር በተባለችው ከተማ ጣራ ላይ የተጠመደ ፈንጂ ለማምከን ሲሞክሩ የሀገሪቱ ፖሊስ አባላት ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

ብዙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ባሉባት ግብጽ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች 10 በመቶ የሚሆነውን ህዝብ ይወክላሉ።

መንግሥት በክርስቲያኖች ላይ መድሎ ይፈጽማል፤ ጥበቃም አያደርግልንም ብለው የሚያስቡም ብዙ የእምነቱ ተከታዮች አሉ።

የክርስቲያኖች ጠባቂ ነኝ በማለት የሚታወቁት ፕሬዝዳንት አልሲሲ፤ የካቴድራሉ እና የአል ፋታህ አል አሊም መስጂድ በተመሳሳይ ሰአት መከፈት "የአንድነት መልእክት ያተላልፋል ብለዋል" በቤተክርስቲያኑ ለተሰበሰቡ የእምነቱ ተከታዮች።

''ሁላችንም አንድ ነን ወደፊትም አንድ ሆነን እንቀጥላለን'' በማለት ነበር መልእክታቸውን ያስተላለፉት።

የሮማው ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ በዚህ አጋጣሚ የተሰማቸውን ደስታና የሰላምታ መልእክት ለአሌክሳንድሪያው ፖፕ ታዋድሮስ ሁለተኛ አስተላለፈዋል።