ኳታር ከነዳጅ አምራች እና ላኪ ሃገራት ማኅበር -ኦፔክ ራሷን አገለለች

ኳታር ከነዳጅ አምራች እና ላኪ ሃገራት ማኅበር ኦፔክ ራሷን ማግለሏን የቡድኑ ስብሰባ ከመደረጉ ከአንድ ቀን በፊት አስታውቃለች።

የባህረ ሰላጤዋ ሃገር ኦፔክን ከ57 ዓመት በፊት የተቀላቀለች ሲሆን፤ ማህበሩን ከሁለት ወራት በኋላ ሙሉ በሙሉ እንደምትሰናበት እና በጋዝ ምርት ላይ እንደምታተኩር አስታውቃለች።

በዓለማችን ከፍተኛ ተፈጥሯዊ ፈሳሽ ጋዝ ለውጪ ገበያ የምታቀርበው ኳታር፤ ጎረቤት ሃገራት ሽብረተኝነትን ትደግፋለች በማለት አግልለዋለታል።

ኦፔክ በዚህ ሳምንት ስብሰባው የነዳጅ ምርት አቅርቦትን እንደሚቀንስ ይጠበቃል።

የኢነርጂ ሚንስትሩ ሳድ አል-ካቢ የኳታርን ውሳኔ ሲያስረዱ ''በነዳጅ ዘርፉ ብዙ አቅም የለንም። የእኛ አቅም ጋዝ ነው'' ብለዋል።

ከባቢያዊ ፖለቲካ ለዚህ ውሳኔ ምክንያት አይደለም ሲሉም የኢነርጂ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

ኳታር ላለፉት 16 ወራት ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ በሌሎች የጎረቤት አገሮች እንደተገለለች ትገኛለች።

ኳታር ከሌሎች የኦፔክ አባል ሃገራት ጋር ስትነጻጸረ አነስተኛ የነዳጅ ምረት አምራች እንደመሆኗ እራሷን ከማህበሩ ማግለሏ በነዳጅ ዋጋ ላይ ዘላቂ የሆነ የዋጋ ልዩነት የመጣል ተብሎ አይታሰብም።

በዚህ ሳምንት በኦስትሪያ ቪየና የሚካሄደው የኦፔክ ስብሰባ ካአሁኑ የበርካቶችን ቀልብ ስቧል።

የኦፔክ አባል ያልሆነችው ሩሲያ፤ በፕሬዚዳንቷ ቭላደሚር ፑቲን በኩል ከሳዑዲ አረቢያው ልዑል አልጋ ወራሽ ጋር የነዳጅ አቅርቦት መጠን ምን ያህል መሆን እንዳለበት ከስምምነት ላይ ደርሰናል ብለዋል።

የፕሬዚዳንት ፑቲን አስተያየት ተከትሎ በነዳጅ ምርት ላይ የዋጋ ጭማሪ አስከትሏል።

ምንም እንኳ የኦፔክ አባል ባትሆንም፤ ሩሲያ ከኦፔክ አባል ሃገራት ቀጥሎ ትልቋ ነዳጅ አምራች ሃገር ነች።

ኳታር በቀን 650ሺ በርሜል ነዳጅ የምታመርት ሲሆን በአንጻሩ ሩሲያ ደግሞ 11.37 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ በቀን ታመርታለች።

አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ኮንጎ፣ ኢኳዶር፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋቦን፣ ኢራቅ፣ ኢራን፣ ኩዌት፣ ሊቢያ፣ ናይጄሪያ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የኦፔክ አባል ሃገራት ናቸው።