በውሽት ሞትኩ ያለው ቻይናዊ ሚስት የራሷንና የልጆቿን ህይወት አጠፋች

ቻይናዊው ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ለልጁ ማሳከሚያ የወሰደው ብድር ዕረፍት ቢነሳው ገንዘብ የሚያገኘበትን አማራጮች ማሰላሰል ጀመረ።

ብዙ አውጥቶ አውርዶ ከአንድ ውሳኔ ላይም ደረሰ። ይሄ ውሳኔው ግን እጅግ የሚወዳቸውን ሚስቱን እና ሁለት ልጆቹን አሳጣው።

ፖሊስ የመዝገብ ስሙ ሂ ነው ያለው ቻይናዊ አባት ዕዳውን ለመክፈል የፈጠረው ዘዴ በአደጋ ምክንያት የሞተ ማስመሰል ነበር። ከዚያም በህይወት መድህን የሚገኘውን ገንዘብ ዕዳውን ሊከፍልበት አስቦ ነበር።

ለዚህ ደግሞ የ34 ዓመቱ ሂ አደጋ የደረሰበት በማስመሰል መኪናውን ወንዝ ውስጥ ይከታል። ፖሊስ የሂን አስክሬን ባያገኘም ሂ ሞቷል ተብሎ ደመደመ።

ይህን እቅዱን ያላወቀችው ባለቤቱ ግን ሂ መሞቱን አመነች። እጅግ ሲበዛም በሃዘን ተጎዳች።

ሃዘኑ እጅግ ቢበረታባት፤ የሦስት እና የአራት ዓመት ልጆቿን እንደያዘች በመኖሪያ አካባቢዋ በሚገኝ ኩሬ ውስጥ ከነልጆቿ እራሷን አሰጠመች።

በዜናው ልቡ በሃዘን የተሰበረው ሂ ባሳለፍነው ዓርብ እጁን ለሚኖርበት ግዛት ፖሊስ ሰጠ።

ሂ ላይ የመድህን ማጭበርበር እና ንብረት ላይ ሆነ ብሎ ጉዳት ማድረስ የሚሉ ክሶች ቀርበውበታል።

ፖሊስ ሂ ባለቤቱን ሳያሳውቅ ከሳምንታት በፊት 145 ሺህ ዶላር የሚያወጣ የሕይወት መድህን ገዝቷል ብሏል።

የቻይና መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ ሂ በሞት ሲለይ ባለቤቱ ወራሽ ሆና ስሟ በመዝገብ ላይ ሰፍሯል።

ከአንድ ወር በፊት ሂ በብድር የወሰደውን መኪና በመጠቀም በአደጋ የሞተ አስመስሏል በማለት የፖሊስ መዝገብ ያስረዳል። ሂ ከአንድ መቾ ሺህ በላይ ዩዋን (የቻይና ገንዘብ) እዳ እንዳለበት ፖሊስ ጨምሮ አሳውቋል።

ሂ የሞተ ባስመሰለ በሶስተኛው ሳምንት የባለቤቱ፣ የአራት ዓመት ወንድ ልጁ እና የሦስት ዓመት ሴት ልጁ አስከሬን ከኩሬ ውስጥ እንዲወጣ ተደርጓል።

ባለቤቱ ከነልጆቿ እራሷን ከማጥፋቷ በፊት ዊቻት በተሰኘው የማሕበራዊ መገናኛ አውታር ላይ 'ከአንተ ጋር ልንቀላቀል እየመጣን ነው'' ብላ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ባለቤቱ ያሰፈረችው መልዕክት ''እኔ የምፈልገው ነገር አራታችንም እንደ ቤተሰብ አብረን እንድንሆን ብቻ ነው'' ይላል።

ሂ ለፖሊስ እራሱን አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ በለቀቀው የቪዲዮ መልዕክት ገንዘቡን የተበደረው የሚጥል በሽታ ያለባት ሴት ልጁን ለማሳከም እንደሆነ እያነባ ያስረዳል።