በምስራቅ ጎጃም መሬት መንሸራተት አደጋ የስምንት የሰዎችን ህይወት ቀጠፈ

በምስራቅ ጎጃም የደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ

የፎቶው ባለመብት, East Gojam zone Communication Bureau

በምስራቅ ጎጃም ዞን፣ ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ፣ እነገት ቀበሌ፣ ወይን ውሃ ጎጥ ነሃሴ 8፣2010 ዓ.ም ከሌሊቱ 6፡30 ገደማ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ በአንድ ቤት ውስጥ የነበሩ ስምንት ግለሰቦች ህይወት አልፏል።

ከሟቾቹ መካከል ስድስቱ የአንድ ቤተሰብ አባል ሲሆኑ፤ አምስት ልጆች እና እናታቸው እንዲሁም ከሌላ አካባቢ በእንግድነት የመጣ የእርሷን ወንድም ጨምሮ ስራ ለማገዝ ሲል በቤቱ የተገኘ ጎረቤት ህይወታቸው እንዳለፈ የምስራቅ ጎጃም ዞን ኮሚዩኒኬሽን ፅ/ቤት ባለሙያ አቶ ጋሻዬ ጌታሁን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የሟቿ ባለቤት ካህን በመሆናቸው በወቅቱ ቤተ ክርስቲያን በመሄዳቸው ከአደጋው ሊተርፉ ችለዋል።

የሟቾቹ የቀብር ስነ ስርዓትም በትናንትናው ዕለት ተፈፅሟል።

በነሃሴ 3፣2010 ዓ.ም በደጀን ወረዳ፣ ቆቅ ውሃ ቀበሌ ላይ ተመሳሳይ አደጋ ደርሶ በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳደረሰ ባለሙያው ይናገራሉ።

በተለይ የክረምት ዝናብ እየጨመረ በመሄዱ ተራራ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልዕክት ቢሮው አስተላልፏል።

በተለይ ወደ ተራራ ጫፍ የሚወጣ ጎርፍ መቀየሻ ቦዮች አቅጣጫቸው እንዲቀየር እየተደረገ መሆኑን አቶ ጋሻዬ ለቢቢሲ ገልፀዋል።