ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በረዷማ ተራራ ላይ ለ7 ቀናት ጠፍቶ የነበረው አውስትራሊያዊ በህይወት ተገኘ
ተራራ መውጣት የሚያዘወትረው የ29 ዓመቱ አውስታራሊያዊ ለሰባት ቀናት በረዷማ ተራራ ላይ ቆይቶ ህይወቱ አለማለፉ ብዙዎችን አስገርሟል።
ኒውዚላንድ ውስጥ የሚገኝ አስፕሪንግ የተባለ ተራራ ላይ ብቻውን ከወጣ በኋላ የት እንደደረሰ አልታወቀም ነበር። የበረዶው ቅዝቃዜ ለህይወት አስጊ ቢሆንም ያለ ማንም ሰው ድጋፍ ለሰባት ቀናት በህይወት ቆይቷል።
ከሰባት ቀናት በኃላ የታደጉት ነፍስ አድን ሰራተኞች ለሰባት ቀናት በረዷማው ተራራው ላይ ቢቆይም ያለ የሌለ ሀይሉን አሰባስቦ የነፍስ አድን ሄሊኮፕተር መጥራቱ አስገራሚ ነው ብለዋል።
የነፍስ አድን ሰራተኞቹ ግለሰቡ ከዚህ ቀደም ወታደራዊ ስልጠና መውሰዱ በህይወት ለመቆየት ሳይግዘው አልቀረም ብለዋል።
የነፍስ እን ሰራተኞቹ፤ አውስትራሊያዊው የተራራውን ግግር በረዶ ቆፍሮ ዋሻ በመስራትና ውስጡ በመሆን ራሱን እንዳተረፈ ይገምታሉ።
ተራራው ላይ በረዶ የቀላቀለ ንፋስ በሰአት 600 ኪሎ ሜትር ይነፍሳል። አውስትራሊያዊው በበረዶው ቅዝቃዜ ሳቢያ ሰውነቱ ከመሸማቀቁ ባለፈ የከፋ ጉዳት አልደረሰበትም።
አውስትራሊያዊው ለነፍስ አድኖች የአደጋ ጊዜ ምልክት ከሰጠ በኃላ ከፍተኛ ንፋስ ስለነበረ በቶሎ ሊደርሱለት አልቻሉም ነበር።
አውስታራሊያዊው ተራራ መውጣት እንደማዘውተሩ ለሁኔታው አመቺ ቁሳቁሶች አንግቦ ነበር። ሆኖም ተራራውን ከወጣ በኃላ ከፍተኛ ንፋስ ስለነበረ ለሰባት ቀናት ያህል ለመውጣት ተቸግሮ ነበር።