የምርጫ ውጤት መገለጹን ተከትሎ በዚምባብዌ ሶስት ሰዎች ተገድለዋል

ዚምባብዌ ታሪካዊ ነው የተባለለትን ምርጫ ካካሄደች በኋላ የምርጫው ውጤት ሲገለጽ በሃገሪቱ አለመረጋጋት የተከሰተ ሲሆን እስካሁን ሦስት ሰዎች ተገድለዋል።

መንግሥት አመጹን ለማረጋጋት በሚል እየወሰደ ያለውን እርምጃ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና መንግሥታት እየተቹ ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግሥታት እና የሃገሪቱ የቀድሞ ቀኝ ገዢ የነበረችው እንግሊዝ በሃገሪቱ መረጋጋት እንዲሰፍን ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን መንግሥት እየወሰደ ካለው እርምጃ እራሱን እንዲቆጠብ ጭምር ጠይቀዋል።

ሮበርት ሙጋቤ ተሳታፊ ባልነበሩበት ምርጫ ገዢው ፓርቲ ዛኑ-ፒኤፍ አሸናፊ መሆኑ ተገልጿል።

ይሁን እንጂ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ዛኑ-ፒኤፍ ምርጫውን አጭበርብሯል ይላሉ።

የገዢው ፓርቲ ዋነኛው ተቀናቃኝ ኔልሰን ቻሚሳ ፕሬዝደንት ኤምርሰን ምናንጋግዋን እንዳሽነፉ አውጀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ፖለቲከኞች ከአመጽ እንዲቆጠቡ የጠየቁ ሲሆን እንግሊዝ አመጹ ''እጅጉን እንዳስሰባት'' አሳውቃለች።

በዚምባበውዌ የአሜሪካ ኤምባሲም ሁሉም አካላት ከአመጽ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ጠይቋል።

የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ቡድን የሆነው አምነስቲ እንተርናሽናል በበኩሉ ተኩስ ከፍተው ህይወት ያጠፉ የመንግሥት ወታደሮች ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ጠይቋል።

ከምርጫው በኋላ ምን ተፈጠረ?

የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ገዢው ፓርቲ ዛኑ-ፒኤፍ የብሄራዊ ምክር ቤቱን መቀመጫ በሁለት ሦስተኛ ማሸነፉን ከገለጸ በኋላ በመዲናዋ ሃራሬ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄዱ።

የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ይህን አይነት የተቃውሞ ሰልፍን መንግሥት ''አይታገሰም'' ሲሉ አስጠነቀቁ።

የተቃዋሚ ጥምር ፓርቲ መሪው ቻሚሳ መንግሥት ወታደሮችን በከተማ ውስጥ ማሰማራቱን እና ህይወት መጥፋቱን አጥብቀው ኮነኑ።

''ወታደሮች የሰለጠኑት በጦርነት ላይ ጠላት እንዲገድሉ ነው። እነኚህ ዜጎች የሃገር ጠላት ናቸውን?'' ሲሉም ጠይቀዋል።

የምርጫ ታዛቢዎች ምን ይላሉ?

የአውሮፓ ህብረት ምርጫው ዘግይቶ ይፋ መደረጉን ኮንኗል።

የመገናኛ ብዙሃን ጣልቃ ገብነት፣ መራጮችን ማዋከብ እና የምርጫ ኮሚሽን ላይ እመነት አለመኖሩን መታዘቡን የአውሮፓ ህብረት ገልጿል።

በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራው የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢ ቡድን በበኩሉ ምርጫው የተካሄደው ''እጅግ በጣም ሰላማዊ በነበረ ሁኔታ ውስጥ ነው። እንዲሁም ምርጫው በፉክክር የተሞላ ነበር'' ብሏል።

የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢ ቡድን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ክስ ማረጋገጥ አልቻልኩም ብሏል።