ሙጋቤ የማይሳተፉበት የመጀመሪያው የዚምባብዌ ምርጫ

ኤመርሰን ምናንጋዋ በዚምባብዌን የነጻነት ትግል ሚና ተጫውተዋል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ኤመርሰን ምናንጋዋ በዚምባብዌን የነጻነት ትግል ሚና ተጫውተዋል

ሮበርት ሙጋቤ ለዘመናት ዚምባብዌን መርተዋል። ባለፈው ዓመት ከስልጣን እስኪወገዱ ድረስም የሀገሪቱ ብቸኛው መሪ ነበሩ።

አሁን ግን ዚምባብዌ ሮበርት ሙጋቤ የማይሳተፉበት ምርጫ ታካሂዳለች። ምርጫው ካሳተፋቸው መካከል አሁን ሀገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲን የሚወክሉት ኤመርሰን ምናንጋግዋና ተቃዋሚው ኔልሰን ቻሚሳ ይገኙበታል።

ለኤመርሰን ምናንጋግዋ የተሰጠው ድጋፍ ከተቀናቃኛቸው የሙቭመንት ፎር ዴሞክራቲክ ቼንጅ መሪ ኔልሰን ቻሚሳ የተወሰነ ብልጫ አሳይቷል ተብሏል።

የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ሮበርት ሙጋቤ በበኩላቸው እሳቸውን ለሚተካ ፕሬዘዳንት ድምጻቸውን እንደማይሰጡ ተናግረዋል።

በሀገሪቷ ታሪክ በምርጫ ሲሳተፉ የመጀመያቸው የሆኑ ወጣቶች ድምጽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል። ለምርጫ ከተመዘገቡት አብዛኞቹ ከ35 ዓመት በታች ናቸው።

በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋሞች ምርጫውን ለመታዘብ ወደ ዚምባብዌ ያቀኑ ሲሆን ተቃዋሚዎች ምርጫው ሊጭበረበር እንደሚችል ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ኔልሰን ቻሚሳ ከተመረጡ በሀገሪቱ ታሪክ ወጣቱ መሪ ይሆናሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኔልሰን ቻሚሳ ከተመረጡ በሀገሪቱ ታሪክ ወጣቱ መሪ ይሆናሉ

ምርጫው ዚምባብዌን ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ውስጥ የከተታት የዓመታት የጭቆና አገዛዝን ተከትሎ የመጣ ነው። የቀደመው አገዛዝ በሀገሪቱ የትምህርት፣ የጤና እንዲሁም የኢንቨስትመንት ዘርፍም እክል ሆኗል። የሀገሪቱ የሥራ አጥነት መጠን 90 በመቶ መድረሱም የአገዛዙ ውጤት ነው ተብሏል።

"አዞው" (በእንግሊዘኛው ዘ ክሮኮዳይል) በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ ያመጡ ይሆናል ተብሎ ይታመናል። ሥራ አጥነትን እንደሚያስወግዱም ቃል ገብተዋል።

የሮበርት ሙጋቤ ደጋፊዎች እንደሆኑ የሚነገርላቸው ቡድኖች በተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ አድርገውባቸዋል።

ተፎካካሪዎቹ ኤመርሰን ምናንጋግዋ እና ኔልሰን ቻሚሳ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ተፎካካሪዎቹ ኤመርሰን ምናንጋግዋ እና ኔልሰን ቻሚሳ

ኔልሰን ቻሚሳ የህዝብ እንደራሴ የሆኑት በ25 ዓመታቸው ነበር። አሁን 40 ዓመታቸው ሲሆን፣ የ75 ዓመቱ ተቀናቃኛቸው ኤመርሰን ምናንጋግዋን አሸንፈው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በዚምባብዌ ታሪክ ወጣቱ መሪ ይሆናሉ።

ከተመረጡ ሀገሪቷ በምጣኔ ሀብት እድገት ቀን እንደሚወጣላት ቃል ቢገቡም እቅዳቸው የተለጠጠ ነው የሚል ትችት ተሰንዝሮባቸዋል።

ከተመረጡ ዚምባብዌ ኦሎምፒክ እንድታስተናግድ ከማስቻል ባሻገር ሀገራቸውን የፈጣን ባቡር ባለቤት እንደሚያደርጓትም ተናግረዋል።

ሮበርት ሙጋቤ ከሁለቱ ተፎካካሪዎች ኔልሰን ቻሚሳን ይደግፋሉ።