ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የደቡብ ሱዳን መንግሥት ለሕዝብ እንደራሴዎቹ መኪና መግዣ 16 ሚሊየን ዶላር ማውጣቱ ቁጣን ቀስቅሷል
ደቡብ ሱዳን ለ400 የሕዝብ እንደራሴ አባላቷ የመኪና መግዣ በሚል ለእያንዳንዱ የ40 ሺህ ዶላር ብድር መስጠቷ የሕዝብ ቁጣን ቀስቅሷል።
የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ 16 ሚሊየን ዶላር የወጣበትን ወጪ ባብራሩበት ወቅት "የሕዝብ እንደራሴዎች በሞተር ሳይክል መሄድ የለባቸውም" ሲሉ ተከራክረዋል።
መንግሥትን የሚተቹ ወገኖች የሕዝብ እንደራሴዎቹ ፕሬዝዳንቱ እስከ 2021 ስልጣናቸውን ማራዘም የሚያስችላቸውን ውሳኔ ካፀደቁላቸው በኋላ ብድሩ የተሰጣቸው እንደ ሽልማት ነው ሲሉ ተችተዋል።
መንግሥት እየተካሄደ ባለው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ምርጫ አይካሄድም ሲል አስታውቋል።
ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የደቡብ ሱዳን ዜጎች በረሃብ አለንጋ እየተሸነቆጡ ሲሆን ለምግብ ቀውሱ በ2013 በሳልቫ ኪር ታማኞች እና በሪክ ማቻር መካከል የተጀመረው ግጭት እንደሰበብ ተደርጎ ይጠቀሳል።
ጦርነቱ 3.8 ሚሊየን ሰዎች ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ቀያቸውን ጣጥለው እንዲሰደዱ ማድረጉን የአለም ምግብ ድርጅት ዘገባ ያሳያል።
የደቡብ ሱዳን ዋና መዲና የሆነችው ጁባ ነዋሪዎች መንግሥት ከልማት ይልቅ መኪና ላይ ገንዘቡን ማዋሉ አስቆጥቷቸዋል።
"በነፍስ ወከፍ 40 ሺህ ዶላር በጣም ብዙ ገንዘብ ነው። ምን አይነት መኪና ቢሆን ነው?" ስትል የምትጠይቀዋ የከተማዋ ነዋሪ የሆነች ግለሰብ "መንግሥት ሕዝቡ ያለበት ሁኔታ ግድ እየሰጠው አይደለም። ይህ ሙስና ነው፤ የህዝብ እንደራሴዎቹ አፋቸውን እንዲዘጉ የተሰጣቸው ይሆን?"ስትል ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ ጠይቃለች።
የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ አቴኒ ዌክ አቴኒ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ይህ በጀት የተያዘለት ጉዳይ ነው። የደቡብ ሱዳንን መንግስትም ገንዘብ አባካኝ ብሎ መውቀስ ''ፍትሃዊ አለመሆን" ነው።
እንደ አቴኒ ከሆነ ይህ ብድር በ2005 እና በ2009 ለሕዝብ እንደራሴዎቹ መኪና ለመግዛት እንደተሰጣቸው ብድር አይነት ሲሆን ብድሩንም በአምስት ዓመት ውስጥ የሚመልሱ ይሆናል።
"መንቀሳቀስ የህዝብ እንደራሴዎቹ መብት ነው" ሲሉም አክለዋል።