በግሪኩ ሰደድ እሳት 74 ሰዎች ህይወታቸውን ካጡ በኋላ የተረፉ ካሉ በሚል ፍለጋው ቀጥሏል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በግሪክ ከሰደድ እሳት የተረፉ ካሉ በሚል ፍለጋው ቀጥሏል። በአቴንስ አቅራቢያ በተከሰተው በዚህ እሳት እስካሁን ድረስ 74 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው ተዘግቧል።
ከፍተኛ ንፋስ እሳቱን ያዛመተው ሲሆን ቤቶቸን እና መኪኖችን አመድ እያደረገ፣ ከሰደዱ ለማምለጥ የሚሮጡትን መግቢያ በማሳጣት ራሳቸውን በአቅራቢያው ወዳለ ባህር እንዲወረውሩ አስገድዷል።
የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሲስ ቲስፕራስ የሦስት ቀን ሐዘን አውጀዋል። ማክሰኞ እለት የ26 አዋቂና ሕፃናት ተቃቅፈው እስከወዲያኛው ያሸለቡ ሰዎች አስክሬናቸው በኮረብታ ጫፍ ለይ ተገኝቷል።
የግሪክ የቀይመስቀል ማህበር ኃላፊ እንዳሉት " ማምለጫ እየፈለጉ ነበር፤ ክፉ እድል ሆኖ ግን ማምለጫ ቀዳዳ አላገኙም፤ እናም መጨረሻቸውን በቅርብ ርቀት ሲያዩት ተቃቀፉ" ሲል ሁኔታውን ገልፀውታል።
ሰኞ እለት ማታ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱን ለማጠፋት በሰዓት 100 ኪሎ ሜትር ከሚምዘገዘግ ንፋስ ጋር ሲታገሉ ነበር።
የድንበር ጠባቂዎች እና የግል ጀልባዎች በውሃ ዳርቻዎች አቅራቢያ የደረሱትን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ማዳን የቻሉ ሲሆን የነፍስ አድን ሰራተኞች በየቤቱ፣ በየመኪናው እና በውሃ ዳርቻዎች በህይወት የተረፉ ካሉ በሚል እየፈለጉ ናቸው። ነገር ግን አሁንም የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት አለ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
በግሪኳ አቲካ እንዲህ ባለ ደረቅ በጋ ሰደድ እሳት የተለመደ ነው።
እንደ አካባቢው ባለስልጣናት ጥርጣሬ ግን የአሁኑ እሳት ሆን ተብሎ በሰዎች የተለኮሰ ሊሆን ይችላል።
ለዚህ ደግሞ ማስረጃቸውን ሲጠቅሱ በአቴንስ ሶስት የተለያየ ስፍራዎች 15 እሳቶች በተመሳሳይ ወቅት መነሳታቸውን ይጠቅሳሉ። ለዚህም ተጠርጣሪዎችን ለመለየት ከአሜሪካ ድሮንን ጠይቀዋል።
ግሪክ እንዲህ አይነት የሰደድ እሳት መቅሰፍት ያስተናገደችው በ2007 ነበር፤ በወቅቱም በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል።















