የፕሬዝዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛን የስልጣን ዘመን እስከ 2034 ሊያራዝም የሚችለው ህዝበ-ወሳኔ ዛሬ ይካሄዳል

የፎቶው ባለመብት, AFP
ውዝግብ ያልተለየው የብሩንዲ ህዝበ-ውሳኔ ዛሬ ይካሄዳል።
በህገ-መንግሥቱ ላይ የሚካሄደው ህዝበ-ውሳኔ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ በስልጣን የሚቆዩበትን ጊዜ እስከአውሮፓዊያኑ 2034 ድረስ ሊያረዝመው ይችላል።
በ2015 ለሶስተኛ ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት መወዳደራቸው በሃገሪቱ ግጭት ከመቀስቀሱም በላይ ያልተሳካ መፈንቅለ መንግሥት እንዲካሄድ ምክንያት ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በህዝበ-ውሳኔው የሃገሪቱን ፕሬዝዳንት የስልጣን ዘመን ከአምስት ወደ ሰባት ከማሳደግ ባለፈ ጠቅላይ ሚንስትር እንዲኖር የሚያደርግ ስርዓት እንዲዘረጋ ወይም አሁን ያለው አሰራር እንዲቀጥል ነው ድምጽ የሚሰጠው።
የመብት ተከራካሪዎች ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ የሚፈልጉት ማሻሻያ ድጋፍ እንዲያገኝ ግጭት፣ ጭቆና እና ፍርሃት እንዲሰፍን ሰርተዋል በሚል ይከሷቸዋል።
ታዛቢዎች ሁኔታው የ2015ቱ ዓይነት ፖለቲካዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል በሚል ስጋታቸወን ያስቀምጣሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ህዝበ-ውሳኔው ላይ ህዝቡ እንዳይሳተፍ ጥሪ ቢቀርብም ይህን ያደረገ ሰው እስከ ሶስት ዓመት የሚደርስ እስራት ይጠብቀዋል ተብሏል።
መንግሥት የሚቀርቡበትን ክሶች በሙሉ ውድቅ አድርጓል።
ባለፈው ወር ብቻ 50 ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መታሰራቸው አንድ የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።
ከቀናት በፊት በሃገሪቱ ሰሜን-ምዕራብ አቅጣጫ በምትገኝ የገጠር መንደር 25 ሰዎች በታጣቂዎች ተገድለዋል።
መንግሥት ቢቢሲ እና ቪኦኤ ላይ የስድስት ወራት እገዳ ጥሎባቸዋል። ቢቢሲ በስደት ላይ የሚገኙ የመብት አቀንቃኝን ሞግቶ አልጠየቀም በሚል ነው እገዳው የተጣለበት።












