ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፈረንሳዩፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ''ትራምፕ በሶሪያ እንዲቆዩ አሳምኛቸዋለሁ'' አሉ
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን እንዳሉት ዶናልድ ትራምፕን ከሶሪያ ጦራቸውን እንዳያሶጡ ይልቁንም ረዘም ላለ ጊዜ በሶሪያ እንዲቆዩ አግባብተዋል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት ትራምፕ በሶሪያ የሚገኘው የአሜሪካንን ጦር በቅርብ ጊዜ እንደሚያሶጡ ተናግረው ነበር።
የሶሪያ መንግሥት በንጹሃን ዜጎቹ ላይ የኬሚካል ጥቃት ፈጽሟል በማለት ባሳለፈነው ቅዳሜ የአሜሪካ፣ የፈረንሳይ እና የእንግሊዝ ጥምር ኃይል የሶሪያ መንግሥት ግዛቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽመዋል።
ማክሮን አስተያየታቸውን ከሰጡ በኋላ፣ የዋይት ሃውስ ቃልአቀባይ ሳራ ሳንደርስ ''የአሜሪካ ተልዕኮ አልተቀየረም- ፕሬዝደንቱ አሁንም ጦሩ በተቻለ ፍጥነት ወደ ሃገሩ እንዲመለስ ይፈልጋሉ'' ብለዋል።
ሳራ ሳንደርስ አክለውም ጽንፈኛው ታጣቂ ቡድን አይ ኤስን ለማጥፋት እና መልሶ እንዳያንሰራራ ለማድግ አሜሪካ ቁርጠኛ አቋም አላት።
አሜሪካ በምስራቅ ሶሪያ ኩርዶችን እና የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ተብልው የሚጠሩ ታጣቂዎችን የሚደግፉ ወደ 2000 የሚጠጉ የጦር ኃይል አባላት አላት።
ኢማኑኤል ማክሮን በቀጥታ የቴሌቪዥን ቃለመጠይቅ ላይ ''ከ10 ቀናት በፊት ፕሬዝደንት ትራምፕ 'አሜሪካ ከሶሪያ ጦሯን ማስወጣት አለባት' ብለው ነበር ይሁን አንጂ በሶሪያ ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት እንዳለባቸው አሳምነናቸዋል።'' ሲሉ ተደምጠዋል።
ማክሮን አክለውም ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው የኬሚካል ጦር ማከማቻ ናቸው ተብለው በሚታመኑ ቦታዎችይ ላይ እርምጃ የመውሰድ አስፈላጊነትን ካሳወቁ በኋላ፤ የሚደረጉ ጥቃቶችም ገደብ ሊኖራቸው እንደሚገባ በስልክ በባደረጉት ውይይት ትራምፕን ማግባባታቸውን ተናግረዋል።
ባሳለፈነው ሳምንት ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ''ሩሲያ ተዘጋጂ፤ ምክንያቱም እየመጣን ነው። ኬሚካል በመጠቀም ዜጎቹን ከሚገድል እና ሃሴት ከሚያደርግ መንግሥት ጋር መወዳጀት አልነበረብሸም'' ብለው ነበር።
የኤሜሪካ፣ የፈረንሳይ እና የእንግሊዝ ጥምር ኃይል ዒላማዎች
የኤሜሪካ፣ የፈረንሳይ እና የእንግሊዝ ጥምር ኃይል ሶስት ዒላማዎች ነበሩት።
የመጀመሪያው ባርዜህ ኮምፕሌክስ ነው። ምንም እንኳ የሶሪያ መንግሥት ቢክድም፤ ይህ ስፍራ የሶሪያ መንግሥት የኬሚካል እና ባይሎጂካል መሳሪያዎች ማምረቻ እና መሞከሪያ ነው ስትል አሜሪካ ትወነጅላለች።
የተቀሩት ሁለቱ ቦታዎች ሆምስ አከባቢ የሚገኙ የኬሚካል መሳሪያ ማምረቻ ስፍራዎች ናቸው።
አሜሪካ 105 የሚሳኤል ጥቃቶች እንደተሰነዘሩ እና ሁሉም ኢላማቸውን እንደመቱ ብትገልጽም ሩሲያ በበኩሏ 71 ሚሳኤሎች ኢላማቸውን ከመምታታቸው በፊት በሶሪያ መንግሥት ተመተው መድደቃቸውን ገልፃለች።