ሕይወት ከኢቦላ ወረርሽኝ በኋላ

ኢቦላ ምዕራባዊ የአፍሪካ ሃገራት የሁኑትን ላይቤሪያ፣ ጊኒና ሲዬራ ሊዮንን ካጠቃ አራት ዓመታትን አስቆጠረ። ሂው ኪንሴላ ካኒንግሃም የተሰኘው ፎቶግራፈር በዚያ ያሉት ነዋሪዎች ሕይወት ከወረርሽኙ በኋላ የደረበትን በፎቶግራፍ ለማንሳት ወደዚያው አቅንቶ ነበር።

እ.አ.አ በ2014 የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ከ1976 ጀምሮ ከተገኙ ቫይረሶች በሙሉ የበለጠ የሰው ሞትን አስከትሎ ነበር።

በላይቤሪያ ዌስት ፖይንት በዝቅተኛ የኑሮ መደብ ላይ ያሉና ዕለተ-ዕለት በሕይወት መቆየት ትግል የሆነባቸው ሰዎችን በቫይረሱ ከተጠቁ መካከል ናቸው።

ዌስት ፖይንት ብዙ ነዋሪዎች ያሉበት የሞንሮቭያ አካባቢ ነው። ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ በማሰብ መንግሥት በአካባቢው የሰዓት እላፊ የጥሎ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ረብሻና ዘረፋ ተስፋፍቶ ነበር።

ኤቫ እና የልጅ ልጇ የሰዓት እላፊውን ከሚቃወሙት ሰዎች መካከል የነበሩ ሲሆን፤ እሱም በፖሊስ ተገድሏል። ''እናትና አባቱ ስለሞቱ ደግሞ እኔ ብቻ ነበርኩ ያለሁት'' ብላ ታስታውሳለች። ''ይመኝ የነበረው ኳስ መጫወትና ሜካኒክ መሆን ነበር'' ትላለች።

ከዓመታት በኋላ ለልጅ ልጇ ሞት መንግሥት በሰጣት የገንዘብ ካሳ የቤተሰቧን ሌሎች አራት ልጆችን አስተምራለች።

ሪታ ካሮል እህቷን በወረርሽኙ ነው የተነጠቀችው። በዌስት ፖይንት መንገዶች ላይ ምግብ በመሸጥ ትተዳደር የነበረ ሲሆን አሁን ግን ገንዝብ በማጠራቀሟ ፍሪጅ ገዝታ በረዶ በመሸጥ የቤተሰቧን የወደፊት ኑሮ እንደምታሻሽል ተስፋ ታደርጋለች።

ኤታ ሮበርትስ በሞንሮቭያ በስተምሥራቅ ባለው በካሕዌህ ክሊኒክ ውስጥ ነርስ ናት። ብዙውን ጊዜ በቀን እስከ 10 የወባና የቆዳ በሽታ ያለባቸውን ታማሚዎች ስታክም ነው የምትውለው።

ክሊኒኩን ያቋቋመው ሬጂናልድ ካሕዌህ ሲሆን፤ ክሊኒኩን የመሠረተበት ዋነኛ ምክንያት እናትና አባቱን በኢቦላ ማጣቱ ነበር። ''ሁሉም ሰው የተሻለ ማህበረሰብን ለመመሥረት እርምጃ መውሰድ አለበት። ይህ ቦታ የሞቱትን ለማስታወስ ነው የተመሰረተው'' ይላል።

የኢቦላ ወረርሽኝ ለላይቤሪያ የጤና ሥርዓት ላይ የጣለው አደጋ አስደንጋጭ ነበር። የሃገሪቱ መሠረተ ልማት ለ14 ዓመታት በቆየው ጦርነት ምክንያት በጣም ተጎድቶ ስለነበር የጤና ማዕከላቱም የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች ለማሟላትም ተቸግረው ነበር።

እንደ ዌስት ፖይንት ያሉ ከፍተኛ አደጋ ላይ የነበሩ አካባቢዎች እስካሁን ድረስ በቅርብ ክትትል ስር ናቸው። ይህም የሆነው ድንገት ያልተለመዱ የጤና ዕክሎች የሚታዩ ከሆነና ሞት ከተከሰተ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በማሰብ ነው። በሳምንት ለ7 ቀናት ሙሉውን 24 ሰዓታት የሚከታተል ሰው ተመድቦ ለየት ያለ ነገር ከተከሰተ ለብሔራዊ የሕዝብ ጤና ተቋም ያሳውቃል።

ጄ ሮበርትስ የሚኖረው የዌስት ፖይንት ፍሳሽ ቆሻሻ በሚያልፍበት ቱቦ አቅራቢያ ነው። ሚስቱን በኢቦላ ካጣ በኋላ የራሱን ሥረ ጀምሯል። ''ሚስቴ ስትሞት አልተቀበረችም፣ ተቃጥላለች። ለዚህም ነው ለዘለዓለም የተለየችኝ የሚመስለኝ። እኔ ደግሞ ትኩረቴን በሙሉ ወደ ልጆቼ አደረግኩኝ። ምክንያቱም ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል።"

ጄ ሮበርትስ ሙቅ ዉሃና የማጠቢያ ሥፍራ ያከራያል። እሱ የሚያቀርበው የውሃ አገልግሎት ለአካባቢው በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም የዌስት ፖይንት የውሃ ፍሳሽ አገልግሎቱ ደካማ ስለሆነ።

በጤና መሠረተ ልማት ብዙ መሻሻያዎች ቢደረጉም፤ ከወረርሽኙ የተረፉ ሰዎች ያለፈውን ትተው የወደፊቱ ላይ በቀና መንፈስ መቀጠል ይፈልጋሉ። ነገር ግን በርካታ ሬሳዎችን ሲቀብሩ የነበሩ ሰዎች አሁን ግራ ግብቷቸዋል።

በኢቦላ የሞቱትን ሰዎች ይቀብሩ የነበሩ ብዙ ሠራተኞች ከዝቅተኛ የኑሮ መደብ የመጡ በመሆናችው የሥራ ዕድል ሲያገኙ ሳያመነቱ ነበር ወደ ሥራው የገቡት።

መሐመድ ካኑ በወረርሽኙ ወቅት የሞቱትን አስከሬኖች ለመቅበር ነበር በመንግሥት የተቀጠረው። ከዚያ ቀጥሎ ግን ምንም ዓይነት ሥራ ስላላገኘ እስካሁን በመቃብሩ ሥፍራ ያለውን ሳር ይከረክማል።

የሞቱትን ለመቀብር በሚደረጉ ሥነ-ሥርዓቶች ላይ አስከሬኖችን መንካት ያስፈልግ የነበረባቸው ጊዜያት ስለነበሩ፤ በሌሎች መገለል ሁሉ ሊያጋጥማቸው ይችላል።

ሞርላ ካግቦ ሌላ የቀብር ሠራተኛ ነው። ''ሰዎች ቤት እንኳን ሊያከራዩን አይፈልጉም ምክያቱም በኢቦላ ጊዜ ከእሬሳ ጋር ንክኪ ስለነበረን''በማለት ያስረዳል።

ሁሉም ፎቶግራፎች ንብረትነታቸው የHugh Kinsella Cunningham ነው።