ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የፖለቲካ ጥያቄ እንዴት ይመለስ?
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ 22 ምሁራን አመልክተው እንደነበር ይታወሳል። ከእነዚህ 13ቱ ተለይተው ስትራቴጂያቸውን እንዲያቀርቡና እንዲያብራሩ ተደርጎ ስምንቱ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ አልፈው ነበር።
እነዚህ ደግሞ ጥር 4 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ በተገኙበትና የምርጫ ኮሚቴው ባስተባበረው የቃለ-መጠይቅ ፓናል መርሀ-ግብር ቀርበው ባገኙት ነጥብ መሰረት አምስቱ ተመርጠው ስማቸው ለዩኒቨርሲቲው ቦርድ መተላለፉን የዩኒቨርሲቲው ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።
ቦርዱም ከቀረቡለት አምስት ተወዳዳሪዎች ሦስቱን በመምረጥ ለመጨረሻ ውሳኔ ለትምህርት ሚኒስቴር አስተላልፏል። በቅርቡም ውጤቱ እንደሚታወቅ ይጠበቃል።
በአገሩቱ ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ላለፉት ወራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በግጭት ሲታመሱ ነበር። በዚህም የተማሪዎች ህይወት አልፏል፤ የአካል ጉዳትም ደርሷል። የመማር ማስተማር ሂደትም ተስተጓጉሏል።
የውድድሩ መጨረሻ ላይ ለደረሱት ሶስቱ ተወዳዳሪዎች ለፕ/ር በቀለ ጉተማ ጀቤሳ፣ ዶ/ር ጀይሉ ዑመር ሁሴንና ፕ/ር ጣሰው ወልደሀና ካህሳይ ቢቢሲ አንድ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።
ለእጩዎቹ ያቀረብነው ጥያቄ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለሚፈጠሩ ግጭቶችና የተማሪዎች የፖለቲካ ጥያቄን ተከትለው ለሚነሱ ተቃውሞዎች መፍትሄ የምትሉት ምንድነው? የውድድሩ አሸናፊ ብትሆኑ እናንተ በምትመሩት ዩኒቨርሲቲ እንዲህ አይነት ነገር ቢፈጠር ምን ታደርጋላችሁ? የሚል ነበር። ፕ/ር ጣሰው ምላሽ ያልሰጡ ሲሆን የሁለቱን እጩዎች ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ዶ/ር ጀይሉ ዑመር ሁሴን
ላለፉት ስድስትና ሰባት አመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የደህንነት ችግር አልነበረበትም ። በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ግን ችግሮች ነበሩ። ችግሩ በሁለት መንገድ ይፈታል ብዬ አምናለው። የዩኒቨርሲቲዎች አለመረጋጋት በተቋማቱ የመልካም አስተዳደር ችግር ሊነሳ ይችላል። አስተዳደራዊ ወይም አካዳምያዊ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለይቶ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል ከውጭ በሚመጣ ግፊት በዩኒቨርሲቲዎች አለመረጋጋት ሊፈጠር ይችላል። ተማሪዎች የህብረተሰቡ አካል ስለሆኑ የህብረተሰቡን ጥያቄ ይዘው ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ሊመጡ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ጥያቄው ምንድን ነው? ችግሩስ? በዩኒቨርሲቲው አቅም ሊፈታ የሚችለው የቱ ነው? የሚለው ላይ መወያየት ያስፈልጋል።
ከዩኒቨርሲቲው አቅም ውጭ ለሆኑት ጉዳዮች ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመለከታቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችና የመንግሥት አካላትን አገናኝቶ የማወያየት ሚና ሊኖረው ይገባል። ሦስተኛው ነገር ዩኒቨርሲቲ ለመንግሥትም ሆነ ለህዝብ ትልቁ የእውቀትና የምርምር ተቋም እንደመሆኑ በፖለቲካው የሚታዩ ችግሮችን በሚመለከት ማወያየት፣ የተለያዩ ሃሳቦች በነፃነት መንፀባረቅ የሚችሉባቸውን መድረኮች ማመቻቸት፣ የመፍትሄ አቅጣጫም የመጠቆም ሥራ መስራት ይኖርበታል ብዬ አስባለው።
ተማሪዎች የህብረተሰቡን ጥያቄ ወደ ዩኒቨርሲቲ በማምጣታቸው ''ለምን?' የሚያስብል ነገር አይኖርም። በእርግጥ የፖለቲካና ፖለቲካ ነክ ጥያቄዎች በዩኒቨርሲቲ አቅም የሚፈቱ አይመስለኝም። ነገር ግን ዩኒቨርሲቲ ተሰሚነቱ ከፍ ያለ ስለሆነ የሚመለከታቸውን ክፍሎች ከተማሪዎች ጋር ሊያወያይ ይችላል። ሌላው ተማሪዎች ጥያቄ እስኪያነሱም ሳይጠበቅ ምርምር አድርጎ የፖሊሲ ለውጥ እንዲመጣ ተፅኖ ማምጣት ይገባዋል። ዩኒቨርሲቲ በህዝብና በመንግሥት መካከል ድልድይ መሆን ይገባዋል።
ፕ/ር በቀለ ጉተማ ጀቤሳ
ተማሪዎች የህብረተሰብ ጥያቄ፣ የፖለቲካ ጥያቄ አያንሱ ሥራቸው መማር ብቻ ነው ማለት አይቻልም። ተማሪ የህብረተሰብ አካል ነው። የተማሪ ንቅናቄም ከበፊት ያለ ነው። ልዩነቱ ድሮ ተማሪዎች አንድ ላይ ሆነው ሥርዓትን ነበር የሚታገሉት። አሁን ግን ተማሪዎች በብሄር ስለሚከፋፈሉ አንድነት አለ ማለት አይቻልም። ባለፉት ዓመታት ስለ ማንነት ፖለቲካ ብዙ ተነግሮ በርካቶች እሱን ያንፀባርቃሉ።
እነዚህ ተማሪዎች ያንን የማንነት ፖለቲካ የተረዱበት መንገድ ለዛሬው ችግር አስተዋፅኦ ያለው ይመስለኛል። ተማሪዎች ማንነታቸው እንዳለ ሆኖ ስለ አገራቸው፣ ስለሰው ክብር፣ ሰብአዊነት፣ እኩልነትና የመሳሰሉ እሴቶች ሊኖሯቸው ይገባል። በዚህ ረገድ ተማሪዎቹ ያለፉበት ትምህርት አንድ ነገር ብቻ በማጉላት ተጠያቂ ይመስለኛል። መስራት የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው።
የትግላቸው ስልት መሆን ያለበት ምንድን ነው? ጉልበትን ማካተት አለበት? እርስ በርስስ በብሄር መከፋፈል ይገባል? ወይስ አንድነታቸውን አጠንክረው ስለፍትህ ስለዴሞክራሲ ማሰብ ይገባቸዋል? በአገሪቱ የመቻቻልና የመደማመጥ ባህል አለ ግን እየተሸረሸረ ሄዷል። እዚያ ላይ መስራት ያስፈልጋል። የመደማመጥ፣ የመወያየትና የሰላም መንፈስን በተማሪዎች መካከል ማስረፅ ያስፈልጋል።
ጥያቄያቸውን ማሰማታቸው ልክ ቢሆንም መንገዳቸውን ማስተካከል ያስፈልጋል።
ዩኒቨርሲቲ ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም። ያለው የፖለቲካ፣ የማህበራዊ ሁኔታ መንግሥት ህዝቡን የሚያዳምጥበትና ለህዝቡ ምላሽ የሚሰጥበት መንገድ ነው ወሳኙ። በዚህ ውስጥ ግን ዩኒቨርሲቲ የራሱ ሚና ይኖረዋል። ወቅታዊውን ነገር ብናይ በመንግሥት በኩል ጥፋት አለ መዘግየትም አለ። ይህ ነገሮችን አባብሷል።
ዩኒቨርሲቲ በመንግሥትና በማህበረሰብ፣ በተማሪም መካከል ግንኙነት ፈጣሪ መሆን ይኖርበታል። ተማሪዎች በተለይም የሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ከሚባለው ትምህርት የሚያገኙት እሴት ምንድን ነው? የሚለው ሊታይ ይገባል። ይህ ለዘላቂ መፍትሄ ሊሰራበት የሚገባ አቅጣጫ ነው።
ዩኒቨርሲቲ ሰውንና የሰው ህይወትን የሚያከብር ዜጋ ነው ማፍራት ያለበት። ተማሪዎች ከጉልበት ይልቅ የመነጋገርና ችግሮችን የመለየት ልምድ እንዲያዳብር ማድረግ የረዥም ጊዜ መፍትሄ መሆን አለበት።
ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትነት እጩ ሆነው ከቀረቡት ሦስት ምሁራን መካከል ሁለቱ አሳሳቢ በሚባለው ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አመለካከትና መፍትሄ ያሉትን ሃሳብ ነበር ከላይ ያቀረብነው።