ሶሪያ ውስጥ 14 የአማፂው ቡድን አባላት በአሳድ ታማኞች መገደላቸው ተነገረ

በአማፂው ቡድን በምትመራው ሶሪያ 14 የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ሠራተኞች ከሥልጣን በወረዱት ባሽር አል-አሳድ ታማኞች ተገደሉ።

በሀገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል ታርቱስ በተባለችው የሜዲቴራኒያን ወደብ በደረሰው "ድንገተኛ" የተባለ ጥቃት 10 ሰዎች መቁሰላቸውም ተሰምቷል።

ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት አማፂያኑ ደማስቆ አቅራቢያ በሚገኘው አስከፊው ሳይድናያ እስር ቤት ኃላፊ የነበረ ግለሰብን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሲሞክሩ ነው ግጭቱ የተነሳው።

ኢስላሚስት ሀያት ታህሪር አል-ሻም (ኤችቲኤስ) የተባለው አማፂ ቡድን ከሁለት ሳምንታት በፊት ነው የአሳድን መንግሥት ገርስሶ ሥልጣን የያዘው።

ሲሪያን ኦብሰርቫቶሪ ፎር ሂዩማን ራይትስ የተሰኘው መቀመጫውን ዩኬ ያደረገ ድርጅት በግጭቱ ከሁለቱም ወገኖች ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።

ድርጅቱ አክሎ ግጭቱ ሲበረታ ተጨማሪ የፀጥታ አባላት ወደ ሥፍራው መላካቸውን ጠቁሟል።

በሌላ ዜና የሶሪያ ባለሥልጣናት ሆምስ በተባለችው የማዕከላዊ ሶሪያ ከተማ ሰዓት ዕላፊ መጣላቸውን ተሰምቷል።

ይህ የሆነው አላዋይት የተባሉት አናሳ ጎሳዎች የእምነት ቦታ ላይ ጥቃት ሲደርስ የሚያሳይ ቪድዮ መለቀቁን ተከትሎ በተነሳ አመፅ ምክንያት ነው።

የሶሪያ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር እንዳለው ቪድዮው የቆየ እና ባለፈው ኅዳር አማፂያኑ አሌፖን ሲቆጣጠሩ የተቀረፀ ነው። ሚኒስቴሩ አክሎ ጥቃቱን ያደረሱት የማይታወቁ ሰዎች ናቸው ብሏል።

ሲሪያን ኦብሰርቫቶሪ ፎር ሂዩማን ራይትስ በቪድዮው ምክንያት በሆምስ ከተማ በተነሳ አመፅ አንድ ሰው ሲገደል አምስት ሰዎች መቁሰላቸውን ዘግቧል።

ከሆምስ በተጨማሪ በታርቱስ እና ላታኪያ ከተማ እንዲሁም የአሳድ መቀመጫ በነበረችው ቃርዳሀ አመፅ ተቀስቅሷል ብሏል።

አላዋይት በሶሪያ አናሳ ጎሳ ከሚባሉ መካከል ሲሆኑ የአሳድ ቤተሰብ ከዚህ ብሔር የመጣ ነው። አብዛኛዎቹ የቀድሞው አገዛዝ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መሪዎች የዚህ ጎሳ አባላት ናቸው።

በኤችቲኤስ የሚመራው ቡድን ቅፅበታዊ ጥቃት የጀመረው ከሰሜናዊው ክፍል ነው። ቀጥሎ በመላ ሀገሪቱ በመስፋፋት የአሳድ የ50 ዓመታት ዘመነ-ሥልጣን እንዲገባደድ አድርጓል።

አሳድ እና ቤተሰቦቻቸው ወደ ሩሲያ ሸሽተዋል።

ኤችቲኤስ ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ በሶሪያ የሚገኙ በርካታ አናሳ ጎሳዎችን እና ኃይማኖቶችን ለመጠበቅ ቃል ገብቷል።

ኢስላሚስት ሀያት ታህሪር አል-ሻም በተባበሩት መንግሥታት፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በአውሮፓ ሕብረት እና በዩናይትድ ኪንግደም አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ ድርጅት ነው።

ባለፈው ማክሰኞ የገና ዛፍ መቃጠሉን ተከትሎ በመላው ሶሪያ አመፅ ተነስቶ ነበር። የሶሪያ አዲሱ አገዛዝ ለአናሳ ጎሳዎች እና ኃይማኖት የተሻለ ከለላ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።