ደቡብ አፍሪካዊቷ ለአራስ እናቶች ልትሸጣቸው እንደነበር የተጠረጠሩ የእንግዴ ልጆችን ሰርቃ ተያዘች

አንዲት ደቡብ አፍሪካዊት የሆስፒታል የጽዳት ሠራተኛ በቦርሳው ውስጥ በርካታ የሰው የእንግዴ ልጅ ተገኝቶባት በቁጥጥር ስር መዋሏን ፖሊስ አስታወቀ።

ሮዝ ምኒሲ የተባለችው ግለሰብ ምፑማላንጋ በምትባለው የደቡብ አፍሪካ ግዛት ውስጥ የተያዘችው የእንግዴ ልጆቹን ሊገዟት የሚችሉ ሰዎችን በማፈላለግ ላይ ሳለች ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ ነው።

"ግለሰቧ በእናቶች ሆስፒታል ውስጥ የጽዳት ሠራተኛ መሆኗ የተረጋገጠ ሲሆን በፖሊስ በተያዘችበት ወቅት የእንግዴ ልጆቹን ይዛ ነበር" ሲል ፖሊስ ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።

የ39 ዓመቷ ግለሰብ የሰው አካል ክፍልን በሕገወጥ መንገድ ይዛ በመገኘት ክስ ባለፈው ሐሙስ ፍርድ ቤት የቀረበች ሲሆን፣ የተያዙባት የእንግዴ ልጆች ለተጨማሪ ምርመራ ለሚመለከተው አካል ተሰጥተዋል።

ግለሰቧ የእንግዴ ልጆቹን ለምን ጉዳይ እንዴት እና ለምን ይዛ እንደተገኘች ለቀረበባት ክስ ምላሽ አልሰጠችም።

ግለሰቧ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው በከተማዋ ውስጥ መደበኛ ቅኝት በሚያደርጉበት ጊዜ አሽከርካሪዎች እንዲያሳፍሯት በምትጠይቅበት ጊዜ ነው።

በቁጥጥር ስር በዋለችበት ጊዜም ብዛታቸው ያልታወቁ የሰው የእንግዴ ልጆችን በፕላስቲክ ቦርሳ ውስጥ ይዛ እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ክስ እንደተመሠረተባት የጠቀሰው ፖሊስ፣ የሚደረገው ምርመራ በመቀጠሉ ተጨማሪ ክሶች በግለሰቧ ላይ ሊቀርብ የሚችልበት ዕድል እንዳለም አመልክቷል።

ነገር ግን ተከሳሿ በሚመጣው ሰኞ ለፍርድ ቤት የዋስ መብት እንዲፈቀድላት ጥያቄ ልታቀርብ እንደምትችል ተገልጿል።

ግለሰቧ ይዛቸው የተገኘችው የእንግዴ ልጆችን ለምን አገልግሎት ሊውሉ ይችሉ እንደነበር ያለው ነገር ባይኖርም በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በአንዳንዶች ዘንድ ከእንግዴ ልጆች ጋር የተያያዘ አመለካከት አለ።

ይህም ምንም እንኳን ሳይንሳዊ ማስረጃ እና ድጋፍ ባይኖረውም አንዳንዶች የእንግዴ ልጅን መመገብ አራስ እናት በርከት ያለ የጡት ወተት እንድታመነጭ ያደርጋታል እንዲሁም ከወሊድ ሊያጋጥም የሚችል መደበት ይከላከላል የሚል እምነት አለ።

በርካታ የእንግዴ ልጆችን ይዛ በፖሊስ የተያዘችው ግለሰብም ለዚሁ አገልግሎት ሊያውሉ ለሚችሉ ሰዎች ልትሸጥ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለ።

በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ አንዳንድ ግድያዎች እና የሰው አካል የመቆራረጥ ወንጀሎች የሚፈጸሙት ከባሕላዊ እምነት ልምምድ ጋር በተያያዘ መሆኑ ይነገራል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንድ ሞዛምቢካዊ የባሕል ሐኪም እዚያው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ትሽዋኔ በተባለች ከተማ የሰው አካል ክፍሎችን ይዞ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር።

በግለሰቡ ላይ በተካሄደ ምርመራ ይዟቸው የተገኙት የሰው አካል ክፍሎች ከሁለት ዓመት በፊት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላ ከተገኘች ሴት አካል ጋር የሚመሳሰል እንደሆነ ተገልጿል።