በአሜሪካ የሰው አስከሬን እንደ ዶሮ እየበለቱ በችርቻሮ የሚሸጡ 'የሬሳ ደላሎች'

አሜሪካዊው ሐሮልድ የ56 ዓመት ጎልማሳ፣ የቴክሳስ ዘናጭ ነበር። ቄንጠኛ ኮፍያ እና ጥብቆ ጂንስ ያዘወትራል። መካኒክ ነው። በእጅ ሙያው ማንም ያውቀዋል።

በአውሮፓውያኑ ኅዳር 2009፣ ካንሰር ተገኘበት። ዘናጩ ሐሮልድ ሞት ከተፍ እስኪል ወደሚቆይበት የእንክብካቤ ማዕከል ገባ።

ሞት ሊወስደው መንገድ በጀመረበት ዋዜማ ሐሮልድን አንድ ጥቁር እንግዳ ጎበኘው። ሞት አይደለም ጥቁሩ እንግዳ። 'ባዮ ኬር የሚባል' ኩባንያ እንጂ።

ይህ ኩባንያ ሐሮልድን ያልተለመደ ጥያቄ ጠየቀው። "ሞትህ አይቀሬ ነው። አንድ ሐሙስ ቢቀርህ ነው። ሰውነትህን አፈር ከሚበላው ለምን ለሕክምና ሳይንስ አትለግሰውም" አለው።

"በተለይ በተለይ ቅልጥምህን እንፈልገዋለን። አንተ ስትሞት ተለማማጅ ሐኪሞች የጉልበት ቀዶ ጥገና ለማድረግ ያስፈልጋቸዋል" አሉት።

ሐሮልድ እሺም እምቢም ሳይል ይሰማቸዋል።

"የሰውነትህን ክፍሎች ለሕክምና መለማመጃ በበጎ ፈቃድ ከሰጠኸን፣ እኛ ደግሞ ያንተን አስከሬን (የተረፈውን) አቃጥለን፣ አመዱን በብልቃጥ አሽገን ለቤተሰብህ እንመልሳለን'' አሉት።

''ይሄን ራስህ ማድረግ ትችላለህ፣ ግን ወጪ አለው። አንተ ሰውነትህን ከሰጠኽን እኛ ቀሪውን ወጪ እንሸፍናለን" አሉት።

በዚህ ንግግር ወቅት ሴት ልጁ አብራው ነበረች። ፋራህ ትባላለች።

"አባዬ ይሄን ሲሰማ ዓይኑ በራ" ስትል የነበረውን ስሜት ታስታውሳለች።

"አባዬ ድርጅቱ ያቀረበለትን ሐሳብ በቤተሰቡ ላይ ያለውን ሸክም እንደሚቀንስ አድርጎ ነበር የተመለከተው። አካሉን መለገስ ደግሞ እሱ ሊያደርግ የሚችለው የመጨረሻው ከራስ ወዳድነት የጸዳ በጎ ነገር አድርጎ ነበር ያሰበው።"

ሐሮልድ ያን ሰሞን ሞተ። ለያውም በገና ዋዜማ።

ሞተ በተባለበት ቅጽበት የ'ባዮ ኬር' ኩባንያ ሠራተኞች ወዲያውኑ ሆስፒታል ከተፍ አሉ። ሞቱን በጉጉት ሲጠብቁት ነበር። አስከሬኑን አፋፍሰው ወሰዱት።

ሴት ልጁ ተጽናናች። ከጥቂት ወራት በኋላ ግን ከፖሊስ ስልክ ተደወለላት።

"ምን ነበር?'' አለች።

የአባቷን ራስ ቅል መጋዘን ውስጥ ተጥሎ አግኝተውት ነበር የደወሉላት። በድንጋጤ ክው ብላ ቀረች።

ፖሊስ በዚህ የሰው አካል በሚበልተው ኩባንያ መጋዘን ውስጥ የ45 ሰዎች የአካል ክፍሎች ተከማችተው አገኝቷል። የአካል ክፍሎቹ ብዛትም ከመቶ ይልቃል።

"ሁሉም አስከሬኖች በመፍለጫ የተቆራረጡ ይመስላሉ" ሲል አንድ መርማሪ ጽፏል።

ፋራህ ይህ ኩባንያ የአባቷን አስከሬን በክብር እንደሚይዘው ገምታ ነበር።

የገዛ አባቷን የራስ ቅል ከተመለከተች በኋላ እንቅልፍ በዓይኗ አልዞር አለ።

"በሌሊት ዓይኖቼን ስጨፍን የተበለቱ አስከሬኖች በቀይ ገንዳ ውስጥ ተጥለው ይታዩኛል። ከዚያን ቀን ጀምሮ በእንቅልፍ እጦት በሽታ እናውዛለሁ'' ትላለች።

ይህ ኩባንያ በጠበቃው በኩል "እኛ የሰው አስከሬን አላንገላታንም" ሲል መልስ ሰጥቶ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ኩባንያው ተዘግቷል። የቀድሞ ባለቤቶቹም ለዚህ ዘገባ አስተያየት ለመስጠት አልፈቀዱም።

ፋራህ እንዲህ ዓይነት ኩባንያ መኖሩን ያወቀችው በሞተው አባቷ ሐሮልድ ምክንያት ነበር።

ከዚያ በፊት የሰው አስከሬን ገዝተው፣ አስከሬን በ'ልተው፣ በመልክ በመልክ ቆራርጠው ለሕክምና ምርምር የሚያቀርቡ "የሬሳ ደላሎች" እንዳሉ በጭራሽ አታውቅም ነበር።

ድርጊቱን በበጎም በክፉም የሚያነሱት አሉ።

ተቺዎች ይህ "ዘመናዊ የመቃብር ዘረፋ ነው" ይላሉ። ሌሎች ደግሞ "የለም ይህ የተቀደሰ ተግባር ነው፤ ዘመናዊ ሕክምና ያለ ሰውነት ልገሳ የትም አይደርስም" ብለው ይከራከራሉ።

እነዚህ የአስከሬን ድለላ የሚሠሩ የግል ኩባንያዎች ለምርምር የሚበቃ በቂ አስከሬን እያቀረቡ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲዎች የሚፈጠረውን ክፍተት እየሞሉ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

ይህ ነገር ስለ ሕይወት እና ሞት ያለንን እሳቤ እና ግንዛቤ የሚሞግት ነው።

ክብር ያለው ሞት እንዴት ያለ ነው? በክብር መሞትስ ምንድነው?

የአስከሬን 'ችርቻሮ ንግድ'

በ19ኛው ክፍለ ዘመን የሕክምና ሳይንስ ጎመራ። አንዳንድ ለሳይንስ በጎ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የገዛ አካላቸው ለሕክምና ቢውል ቅር እንደማይላቸው በይፋ መናገር ጀመሩ።

ኑዛዜያቸውም ሃብት እና ንብረቴን ብቻ ሳይሆን ሰውነቴንም ለሕክምና ምርምር ይዋልልኝ የሚል ሆነ።

ብራንዲ ሽሚት በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሰውነት ክፍሎች የልገሳ ክፍል ዳይሬክተር ነው። ካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ በዚህ ተግባር ይታወቃል።

ብራንዲ ባለፈው ዓመት ማዕከላቸው 1,600 "የሙሉ አካል ልገሳ" እንደተቀበሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አካላቸው ተ'በልቶ ለምርመራ እንዲውል የፈቀዱ ሌሎች 50,000 ሰዎች አሉ። እነዚህ አስቀድመው የተመዘገቡ ናቸው። ገና ያልሞቱ።

ብዙውን ጊዜ የሰውነት ልገሳ ራስን ለሌሎች አሳልፎ ከመስጠት ስሜት የሚመነጭ ነው ይላሉ። "ብዙዎቹ አስከሬናቸውን የሚለግሱ ሰዎች በጣም የተማሩ ወይም ለዕውቀት ከፍ ያለ ፍላጎት ያላቸው ናቸው።"

ብራንዲ ጨምረው እንዳብራሩት እዚህ በጎነት ላይ ገንዘብ የተወሰነ ሚና አለው።

ለብዙ ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት ከባድ ወጪ ነው። ይህ ወጪ እንደሚሸፈንላቸው ሲያውቁ አስከሬናቸውን በነጻ ለመስጠት ይፈቅዳሉ።

የአስከሬን ሸማቾች እነማን ናቸው?

እንደ አብዛኞቹ የሕክምና ትምህርት ቤቶች ሁሉ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በሰውነት ልገሳ መርሐ ግብር ከአስከሬን ትርፍ አያገኝም። አስከሬኖች ወይም በሕክምና ቋንቋ ካዳቫስ (cadavers) እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ጥብቅ መመሪያዎች አሉት።

ነገር ግን ከቅርብ አሥርታት ወዲህ፣ በአሜሪካ አንድ አወዛጋቢ ነገር ተፈጥሯል።

ከግለሰቦች የአስከሬን እየገዙ የሚ'በልቱ፣ ከዚያም ልክ እንደ መኪና መለዋወጫ የሚያከፋፍሉ ለትርፍ የተቋቋሙ ኩባንያዎች ተፈጥረዋል።

ድርጅቶቹ እራሳቸውን "ሁነኛ የሰውነት ክፍሎች ማከማቻ ኩባንያ" ብለው ቢጠሩም ሕዝብ ይበልጥ የሚያውቃቸው ግን 'የሬሳ ደላሎች' በሚል ነው።

ከደንበኞቻቸው መካከል ዩኒቨርስቲዎች ይገኙበታል። አስከሬኖቹን የሚገዟቸው ሐኪም ሊያለጥኑባቸው ነው። ለእነርሱ አንድ የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ እንደመግዛት ሊሆን ይችላል።

ሌሎች ደንበኞቻቸው ደግሞ በሕክምና ምሕንድስና ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው። ለምሳሌ የዳሌ ንቅለ ተከላ ምርቶችን ለመሞከሪያ አስከሬኖችን ይፈልጋሉ።

እንዲህ ዓይነት ለትርፍ የሚሠራ 'የአስከሬን ድለላ ሥራ' በዩናይትድ ኪንግደምም ሆነ በአውሮፓ በጥብቅ የተከለከለ ነው። በአሜሪካ ግን ሕጉ ልል ስለሆነ ቢዝነሱ እየጎመራ ሄዷል።

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2017 ብሪያን ግሮው የተባለ ስመ ጥር የሮይተርስ ጋዜጠኛ በዚህ ዙሪያ አንድ ምርመራ አጠናቅሮ ነበር።

የእርሱ ዘገባ እንደሚያስረዳው ለትርፍ የተቋቋሙ የአስከሬን ድለላ ሥራ የሚሠሩ 25 ኩባንያዎች በአሜሪካ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ኩባንያ ብቻ በሦስት ዓመት 12 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ አስመዝግቧል።

ለትርፍ የተቋቋመው የአካል ክፍል ንግድ በዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎች የአውሮፓ አገራት ውስጥ በትክክል የተከለከለ ነው፤ ነገር ግን በአሜሪካ ውስጥ ያለው ልቅ የሆነ ደንብ ንግዱ እንዲያብብ አስችሎታል።

በዚህ የአስከሬን ድለላ ሥራ ብዙ ኩባንያዎች እየከበሩ ናቸው።

በርካቶች ጥብቅ የሥነ ምግባር መመሪያን ይከተላሉ። አንዳንቹ ግን አስከሬን በማንገላታት። የሟች ቤተሰቦችን በማንቋሸሽ እና አቅመ ደካሞችን በሐዘናቸው ላይ በመዘባበት ስማቸው ይነሳል።

ንግዱ ከሌሎች አገራት በላይ በአሜሪካ ሊጎመራ የቻለው "በቁጥጥር ልልነት ምክንያት ነው" ስትል ጄኒ ክሌማን ትናገራለች።

ጄኒ በጉዳዩ ዙሪያ 'ዘ ፕራይስ ኦፍ ላይፍ' 'The Price of Life' የሚል መጽሐፍ ጽፋለች።

ጄኒ በመጽሐፏ በርካታ አገራት ከአሜሪካ የአስከሬን ግዥ እንደሚፈጽሙ ደርሳበታለች።

"በብዙ አገሮች የልገሳ እጥረት አለ። ስለዚህ እጥረቱን ለማካካስ አስከሬን የሚያገኙት ከአሜሪካ ነው" ትላለች።

የአስከሬን ደላሎች መደበኛ ምዝገባ አያካሄዱ ይሆናል። ስለዚህ ይፋዊ አሃዝ ለማግኘት አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ሮይተርስ እንደሚለው ከአውሮፓውያኑ 2011 እስከ 2015 ድረስ ብቻ በአሜሪካ ያሉ የግል ደላሎች ቢያንስ 50 ሺህ አስከሬኖችን ተቀብለው ከ182 ሺህ በላይ የሰውነት ክፍሎችን አሠራጭተዋል።

ይህ አምቡላንሶችን የሚያሳድዱት ስግብግብነት ብዙ እያነጋገረ ነው።

ነገሩ ቢዝነስ መሆኑ የፈጠራቸው ከሰውነት ሞራል ጋር የሚቃረኑ ተግባሮች አሉ።

ለምሳሌ ሮይተርስ ባደረገው ምርመራ ቀብር አስፈጻሚ ኩባንያዎች ከአስከሬን ደላሎች ጋር የሥራ ቁርኝት ፈጥረዋል።

ቀብር አስፈጻሚዎች ደላሎቹን ሊሞት ከተቃረበ ሰው ቤተሰብ ጋር ያስተዋውቋቸዋል። ከዚያ ኮሚሽን ያገኛሉ። ኮሚሽኑ እስከ 1ሺህ ዶላር ይጠጋል።

እነዚህ ደላሎች ከሥራ ቢወጡስ?

በዚህ ጉዳይ ላይ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁሉ አሜሪካ ጥብቅ ሕግ ማውጣት አለባት ይላሉ።

ምን ዓይነት ሕግ የሚለው ግን ያጨቃጭቃል።

የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲዋ ባልደረባ ሽሚት አሜሪካ የአውሮፓውያንን ሕግ ዓይነት ማውጣት አለባት ይላሉ። ይህ ደግሞ አስከሬንን ለትርፍ ማዋል የሚከለክል ነው።

በጉዳዩ ላይ መጽሐፍ የጻፉት ክሊማን ግን ይህ ሕግ ከወጣ ከፍተኛ የአስከሬን እጥረት ይፈጠራል ይላሉ።

"የአውሮፓ ዓይነት ጥብቅ ሕግ ማውጣት ካለብን መጀመሪያ በርካታ ሰዎች በፈቃደኝነት አስከሬናቸው ለሳይንስ ምርምር እንዲውል እንዲፈቅዱ ማሳመን ያሻል" ይላሉ።

ሌላው ተስፋ የኢ-ነባራዊ ገጽታ (Virtual Reality) ሳይንስ እየተመነደገ መሄድ ነው። ይህ ከሆነ ምናልባት ለሳይንስ ምርምር አስከሬኖች ላያስፈልጉ ይችላሉ።

ተማሪዎች በኢ-ነባራዊ ገጽታ ማንኛውንም ምርምር ማድረግ የሚችሉበት ዕደል ይፈጠራል።

በ2023 ኬዝ ዌስተርን ዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹ ሙሉ በሙሉ አስከሬን ትተው በኢ-ነባራዊ ገጽታ የሚታገዝ ኮምፒውተር ወለድ የሰው አካል ላይ ምርምር እንዲያደርጉ አድርጎ ተሳክቶለታል።

ሌሎች ዩኒቨርስቲዎችም ይህን ፈለግ ይከተሉ ይሆናል። እስከዚያው ግን የአስከሬን ደላሎች ቢዝነስ እየጎመራ መቀጠሉ የማይቀር ይመስላል።