ወደፊት ሊከሰት የሚችለው ‘ወረርሽኝ ኤክስ’ ምንድን ነው? ከኮቪድ የበለጠ ሕዝብ ሊጨርስ ይችላል?

የዓለም የምጣኔ ሃብት ጉባኤ በዳቮስ፣ ስዊትዘርላንድ ባለፈው ሳምንት ተካሂዷል።

ጎን ለጎን የዓለም ጤና የሚያሳስባቸው ትልልቅ መሪዎች በር ዘግተው ለቀናት መክረዋል።

እንደ ኮቪድ ያለ አዲስ ወረርሽኝ ከመምጣቱ በፊት ምን ይደረግ? እንዴት እንዘጋጅ በሚለው አጀንዳ ነው የተወያዩት።

ለጊዜው መጪውን ወረርሽኝ ስሙን “በሽታ ኤክስ” በሚል ይዘውታል።

የዓለም ጤና ድርጅት ከእንግዲህ መዘናጋት የለም፤ ለመጪው ወረርሽኝ መዘጋጀት የግድ ነው ሲል ነበር። ምክንያቱም የኮቪድ ወረርሽኝ ዓለም ላይ ያደረሰው ጠባሳ፣ አገራትን ያስከፈለው ዋጋ ቀደም ብሎ ዝግጅት ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ይህን ያህል አይሆንም ነበር ይላሉ፤ ጤናውን ዘርፍ የሚመሩት።

ዓለምን ትሪሊዮን ዶላር ያከሰራት ኮቪድ የሕክምና መሠረተ ልማት ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ቢሆን ኖሮ ውድመቱ ቢያንስ ይቀንስ ነበር ይላል የዓለም ጤና ድርጅት።

“በሽታ-ኤክስ’’ ምንድነው?

በሽታው በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ያለ ሳይሆን፣ ወደፊት ሊመጣ ይችላል ተብሎ የሚገመት ወረርሽኝ ነው።

ለዚያም ነው ቁርጥ ያለ ስም ሳይሰጠው በ”ኤክስ” ፊደል የተወከለው።

ምናልባት ከአንድ አገር ተነስቶ አህጉር የሚያቋርጥ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ በተወሰኑ አገራት ጉዳት አድርሶ ሥርጭቱ ሊገታ የሚችል ይሆናል።

ይህ ስያሜ ኮቪድ ከመምጣቱ በፊትም ነበር፣ ለነገሩ። የዓለም ጤና ድርጅት በአውሮፓውያኑ ጥር 2018 ስሙን ጠቀስ አድርጎት ነበር።

በዓለም ጤና ድርጅት አንድ ክፍል አለ። ዋና ሥራው አዳዲስ ሊከሰቱ ለሚችሉ ወረርሽኞች ቀድሞ መዘጋጀት እና መሠረተ ልማቱን ማሰናዳት ነው።

በወረርሽኝ ጊዜ ደግሞ ጥናትና ምርምር ማድረግ እና ለበሽታው የክትባት ሙከራዎችን ማድረግ፣ መድኃኒት መዘጋጀትን ይጨምራል። ዋንኛ ሥራው አንዳች ወረርሽኝ ሲከሰት ቶሎ ሥርጭቱን መግታት ነው።

በቅርብ ዘመን ብዙ ወረርሽኞች ተቀስቅሰው ተመልክተናል።

ሳርስ፣ ስዋይን ጉንፋን፣ ኢቦላ እና ኮቪድ የቅርብ ጊዜ ትዝታዎች ናቸው።

የሚቀጥለው ዓለም አቀፍ ወረርሽን ምን ይሆን የሚለው ባለሙያዎችን ከወዲሁ ማወያየት የጀመረውም ለዚሁ ነው። የጤና ባለሙያዎች መጪው ወረርሽኝ ምናልባት ከእስከዛሬው ሁሉ የከፋ ይሆናል የሚል ፍርሃት አላቸው።

“በሽታ ኤክስ’’ ወረርሽኝ ይሆናል?

ባለፈው ሳምንት በነበረው የዓለም የምጣኔ ሃብት ጉባኤ ላይ አንድ ውይይት ተደርጎ ነበር።

ውይይቱን የመሩት የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ ነበሩ።

የውይይቱ ርዕስ “ለበሽታ ኤክስ መሰናዳት” ይሰኛል።

ውይይቱ ያተኮረው ወደፊት ከኮቪድ የከፋ ወረርሽኝ ቢከሰት የጤና መዋቅሩ በቶሎ እንዲመክት እንዴት መዘጋጀት ይቻላል የሚል ነበር።

ዶ/ር ቴድሮስ በውይይቱ ላይ ሲናገሩ “አንዳንድ ሰዎች በሽታው ገና ሳይከሰት ለገዳይ ወረርሽኝ መዘጋጀት ፍርሃትን ሊፈጥርባቸው ይችላል። ነገር ግን የሚያዋጣን በቂ ዝግጅት ማድረግ ነው፤ በሰው ልጅ ታሪክ ብዙ ወረርሽኞች ተከስተዋል፤ ወደፊትም ይከሰታሉ” ብለዋል።

የኮቪድ ወረርሽኝ ብዙዎች የጠበቁት አልነበረም። ነገር ግን የወረርሽኝ ባለሙያዎች ይህ ነገር ቀድሞ ሊከሰት እንደሚችል ሲያስጠነቅቁ ነው የኖሩት።

ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከል ብዙዎቹ አሁንም ቀድሞ ከእንሰሳት የሚመነጭ ወረርሽኝ ያሰጋቸዋል።

እስከ ዛሬ ከተከሰቱ ወረርሽኞች 75 በመቶዎቹ የሚሆኑት እንሰሳት ወለድ (zoonotic) ናቸው። በሌላ አነጋገር ከእንሰሳት ወደ ሰው የተላለፉ ናቸው።

ኮቪድም እንደዚያ ነው። ቻይና ዉሃን ከሚገኝ የእንሰሳት እርድ ገበያ ወደ ሰው እንደተላለፈ ነው የሚገመተው። የሰው ልጆች ባህሪ፣ የአየር ንብረት መለወጥ፣ የሰው ልጆች ከቦታ ቦታ በፍጥነት መንቀሳቀስ፣ በዱር እንሰሳት አካባቢ የሰው ልጆች መገኘት እና ኑሯቸውን ማወክ እንሰሳት ወለድ ወረርሽ እንዲወለድ ሊያደርግ ይችላል ይላሉ ባለሙያዎች።

የከተሞች መስፋፋት፣ የሕዝብ ብዛት በፍጥነት መጨመር፣ የንግድ መቀላጠፍ በተለይ ወረርሽኞች ሲነሱ በቀላሉ ዓለምን እንዲያዳርሱ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ይላሉ ባለሙያዎች።

ዓለም ለመጪው ወረርሽኝ ምን ያህል ተዘጋጅቷል?

በዳቮስ የዓለም የምጣኔ ሃብት ጉባኤ ላይ ዶ/ር ቴድሮስ መሥሪያ ቤታቸው ለመጪው ወረርሽኝ ከወዲሁ መሰናዶ መጀመሩን አብስረዋል።

ይህ የወረርሽኝ ፈንድ እና የቴክኖሎጂ ልውውጥ ማዕከልን መክፈት ይጨምራል። ሁለቱ ማዕከላት በደቡብ አፍሪካ ነው የተከፈቱት። አንዱ ዕቅድ በዚያው ማዕከል ክትባት እንዲመረት ማስቻል ነው። ሌላው መጪው ዕቅድ ደግሞ በሃብታም እና ድሃ አገራት መሃል የክትባት ሥርጭትን ፍትሃዊ ማድረግ ነው።

በኮቪድ ጊዜ በዚህ ረገድ ብዙ ክፍተቶች እንደነበሩ ይታወሳል።

የአውሮፓ ኅብረት የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከል ባለሥልጣናት በአውሮፓውያኑ 2022 ባወጣው አንድ ሪፖርት፣ አዲስ የጤና መሠረተ ልማት ለመዘርጋት ከመሞከር ይልቅ ያለውን ማጠናከር ወረርሽኝን ቶሎ ለመግታት ይረዳል ብሎ ነበር።

የሚዘረጉ መሠረተ ልማቶች እና የጤና ሥርዓቶች ወረርሽኝ ከመምጣቱ በፊት ሊፈተሹ ይገባልም ብሏል።

በ2022 የዓለም ጤና ድርጅት 10 ምክረ ሐሳቦችን አሳትሞ ነበር። እነዚህ ምክረ ሐሳቦች በተፋጠነ ዘዴ የጤና መረጃን እንዴት መሰብሰብ እና መጋራት ይቻላል፤ እንዴትስ መተንተን ይቻላል የሚለውን ጉዳይ የሚያብራራ ነው።

“የተሳለጠ የበሽታ ቅኝትና ክትትል ዘዴ (disease surveillance system) ወረርሽኝ ሲከሰት ቶሎ እንዲደረስበት ያስችላል። ወረርሽን ከተዛመተ በኋላ የብዙዎን ሕይወት ያሳጣል፤ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፤ መቆጣጠሩም ከአቅም በላይ ይሆናል” ይላል ከምክረ ሐሳቦች አንዱ።

የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኞች ሁልጊዜም ከሚታወቅ ምንጭ ይነሳሉ ብሎ አያምንም። አንዳንድ ጊዜ ለሰው ልጅ ግልጽ ባልሆኑ እና መኖራቸው እንኳ በማይታወቁ በሽታ አምጪ ተህዋስ (pathogen) ሊነሳ ይችላል።

ለዚህ መፍትሄው ብዙ ሰዎች የክትባት ቴክኖሎጂን ማሳደግ እና ማዘመን ነው ዋናው ብለው ያምናሉ።

በርካታ የኮቪድ ክትባቶች የተመረቱት ወረርሽኙ በተከሰተ በዓመቱ ነው። ይህ በሕክምና ታሪክ አስደናቂ የሚባል ነው።

ወደፊት ሳይንቲስቶች ጊዜን ለመቆጠብ ከዚህ ቀደም ከተመረቱ ክትባቶች በአጭር ጊዜ አቀነባብሮ አዲስ ክትባት የሚፈጠርበትን መንገድ ሊያስቡ ይገባል። ልክ ምግብን ለማሰናዳት መሠረታዊ የሚባሉ አስቤዛዎች እንደሚያስፈልጉ ሁሉ ማለት ነው።

ይህ ሲሆን ነው በአጭር ጊዜ የወረርሽ ሥርጭትን መግታት የሚቻለው፤ አይበለውና ‘በሽታ ኤክስ’ ወረርሽኝ ከተፈጠረ። አለዚያ ‘ወረርሽን ኤክስ’ በሚያደርሰው ጥፋት ኮቪድን የሚያስንቅ ሊሆን ይችላል።