በአሜሪካ አደገኛ ነው የተባለ ፈንገስ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዛመተ ነው ተባለ

በአሜሪካ ካንዲዳ ኦረስ የተባለ ፈንገስ በስፋት እየተዛመተ ነው ሲል የአገሪቱ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) አስታወቀ።

ይህ የፈንገስ ኢንፌክሽን ሰዎችን አንዴ ከያዘ ገዳይ ነው፤ ለማከም መድኃኒት በተሰጣቻው ታማሚዎች ላይ ለውጥ አልታየም።

ይህ 'ፈንጋል ኢንፌክሽን' ከአውሮፓውያኑ 2021 ጀምሮ በአሜሪካ ብቻ የተጠቂዎች ቁጥር ከ756 አሁን ወደሚገኝበት 1ሺህ 471 ደርሷል።

ጤነኛ ሰዎች በዚህ የፈንገስ በሽታ አይጠቁም።

ይሁንና ሆስፒታል አካባቢ በተለይም በጽኑ የሕሙማን ክፍል የሚገኙ፤ በሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ (ቬንትሌተር) እገዛ የሚተነፍሱ፣ እንዲሁም የበሽታ መከላከል አቅማቸው የተዳከሙ ሰዎች ለዚህ የተጋለጡ ናቸው።

በተለይም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ለካንዲዳ ፈንገስ ተጋላጭ ናቸው።

በዚህ የፈንገስ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ብዙዎቹ ለሚሰጣቸው የፀረ ፈንገስ መድኃኒት ምላሽ አይሰጡም። በዚህ የተነሳም አንዴ ከተያዙ ለመፈወስ አይችሉም።

ይህም በመሆኑ ነው የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) በማገገሚያ ማዕከላት እና በሆስፒታሎች ውስጥ ልዩ ጥንቃቄ እንዲደረግ ያዘዘው።

በዚህ የፈንገስ ተህዋሲ የተያዙ ሰዎች የሚሰጣቸው መድኃኒት ኢቺኖካንዲንስ (echinocandins) የተባሉ ሲሆን፣ ነገር ግን አብዛኞቹ ታማሚዎች መድኃኒቱ አልሠራላቸውም።

ለዚህ ፈንገስ መዛመት ዋና ምክንያት ተብሎ የተቀመጠው በሆስፒታሎች አካባቢ የሚታይ ደካማ የሆነ የኢንፌክሽን መከላከል ተግባር ነው።

ሌላው ምክንያት ደግሞ በኮቪድ ተህዋሲ መዛመት የተነሳ በተፈጠረ መጨናነቅ የጤና ማዕከላት ተገቢውን የንጽሕና እና መሣሪያዎቸን የማጽዳት ሂደትን መከተል በማቆማቸው ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

ከአሜሪካ በተጨማሪ በሌሎች አገሮችም ካንዲዳ ኦረስ ፈንገስ ታይቷል።

ባለፈው ዓመት የዓለም ጤና ድርጅት ይህን ፈንገስ “በመዛመት ቅድሚያ የያዘ አደገኛ ኢንፌሽክሽን” ሲል መድቦት ነበር።