ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፀጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ የተጠቀሙበት የጦር ጉዳተኞች ሰልፍ በመቀለ
ባለፉት ዓመታት በተካሄደው እና በቅርቡ በሰላም ስምምነት መቋጫ ባገኘው ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው የትግራይ ተዋጊዎች ያሉበት ሁኔታ እንዲስተካከል በመጠየቅ መቀለ ውስጥ አደባባይ መውጣታቸው ተዘገበ።
ከመቀለ ከተማው ዳርቻ ተነስተው ወደ መሃል ከተማዋ ያመሩት ሰልፈኞች ከክልሉ ባለሥልጣናት ጋር የተነጋገሩ ሲሆን የፀጥታ ኃይሎች ሰልፈኞች ለማስቆም አስለቃሽ ጋዝ መጠቀማቸውም ተዘግቧል።
የጦር ጉዳተኞቹ እንዲቆዩ በተደረገበት ማዕከል ውስጥ አስፈላጊውን የሕክምና ድጋፍ እንዲሁም በቂ ምግብ እና አልባሳት ስለማይቀርብላቸው በችግር ውስጥ መሆናቸውን በመግለጽ ነው ለሰልፍ የወጡት።
በስፍራው የነበሩ ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የፀጥታ ኃይሎች የጦር ጉዳተኛ የሆኑት ሰልፈኞች ከነበሩበት ቦታ በመውጣት ወደ መሃል መቀለ እንዳይሄዱ ለማስቆም ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም።
የክልሉ ቴሌቪዥንም የጦር ጉዳተኞቹ በቂ የሕክምና ድጋፍ እና የምግብ አቅርቦት በመጠየቅ ሰላማዊ ሰለፍ ማድረጋቸውን ዘግቧል።
ለሰልፍ የወጡት የጦር ጉዳተኞች የተለያዩ የአካል ድጋፍ የሚጠቀሙ መሆናቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገረው፣ በመቀለ ምሥራቅ ከሚገኘው ኩሓ መለስ ካምፓስ ከተባለ ስፍራ በመነሳት ተቃውሟቸውን ለማሰማት ያቀኑት ወደ የክልሉ መስተዳደር ጽሕፈት ቤት ነበር ብለዋል።
ሰልፈኞቹን ለመበተን የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ሙከራ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ጭምር የታገዘ እንደነበር የዐይን እማኞች የተናገሩ ሲሆን፣ ነገር ግን ሰልፉ ቀጥሎ ወደ ክልሉ መስተዳደር ጽህፈት ቤት ለመድረስ ችለዋል።
እዚያም ከቀናት በፊት አዲስ የሚመሠረተውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሩ በህወሓት የተሰየሙት እና የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑትን አቶ ጌታቸው ረዳን አግኝተው ማነጋገራቸው ተገልጿል።
የጦር ጉዳተኛ ሰልፈኞቹም ያሉባቸውን ችግሮች ለባለሥልጣኑ ያስረዱ ሲሆን፣ አቶ ጌታቸውም በሁኔታ ማዘናቸውን በመግለጽ የቀረቡት ችግሮች በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲያገኙ እንደሚደረግ በመግለጽ በተሽከርካሪዎች ወደመጡበት እንዲመለሱ ማድረጋቸው ተዘግቧል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በመቶ ሺህዎች መሞታቸው እና በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ የተለያየ ዓይነት ጉዳት እንደደረሰባቸው ይነገራል።
በጦርነቱ ከቆሰሉት መካከል አንዱ ለቢቢሲ ትግርኛ እንደተናገረው፣ ባለው የመድኃኒት እና የሕክምና መሳሪያዎች እጥረት ምክንያት በቂ የሕክምና እንክብካቤ እና ድጋፍ እየተደረገልን አይደለም ብሏል።
ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሃት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ጦርነቱ ከቆመ ከአራት ወራት በላይ ሆኖታል።
በዘላቂነት ግጭትን ለማስቆም በተደረሰው ስምምነት መሠረት የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ እና ወደ ተሃድሶ እንዲገቡ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በክልሉ ውስጥ ያሉ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች እንዲወጡ ተወስኗል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የሰብአዊ እርዳታ እና የሕክምና መገልገያዎች ወደ ክልሉ እንዲገቡ የተደረገ ቢሆንም፣ በቂ እንዳልሆነ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።