ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኒጀር፡ መፈንቅለ መንግሥቱ ካልቆመ ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ ሲል ቀጠናዊ ድርጅት አስጠነቀቀ
የምዕራብ አፍሪካ አገራት በኒጀር ወታደራዊው ቡድን በመፈንቅለ መንግሥት መንበረ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ ወታደራዊ እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ አስጠነቀቁ።
መሪዎቹ ወታደራዊው ቡድን በ7 ቀናት ውስጥ በኃይል ከስልጣናቸው የተነሱትን ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዙማን ወደ ስልጣን እንዲመለስ አሳስበዋል።
ከቀደም ሲል መፈንቅለ መንግሥት ፈጻሚዎቹ ኒጀር ላይ ጫና ለማድረግ የሚጥር ቀጠናዊውም ይሁን ምዕራባውያን አገራትን ከመጋፈጥ ወደ ኋላ አልልም ብሎ ነበር።
የምዕራብ አፍሪካ አገራት ስብስብ የሆነው ኢኮዋስ አባል አገራት በኒጀር የተከሰተውን ቀውስ በማስመልከት በናይጄሪያ ስብሰባ ተቀምጠው ነበር።
ከስብሰባው በኋላ ኢኮዋስ ለመፈንቅለ መንግሥት ምንም አይነት ትዕግስት የለኝም ያለ ሲሆን “ሕገ-መንግሥታዊ መረጋጋትን ለመፍጠር አስፈላጊ የሆኑ ሁሉንም እርምጃዎች እወስዳለሁ” ብሏል።
"ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል ኃይልን ሊጨምር ይችላል” ያለ ሲሆን ለዚህ እቅድ ተግባራዊነት የአገራቱ የጦር መሪዎች እቅድ ለማውጣት ተገናኝተው ይነጋገራሉ ብለዋል የኢኮዋስ አባል አገራት በመግለጫቸው።
ባሳለፍነው ሳምንት የኒጀር ፕሬዝዳንት የክብር ዘብ ኃላፊ የተመራ ወታደራዊ ቡድን በፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዙም ላይ መፈንቅለ መንግሥት መፈጸሙ ይታወሳል።
የመፈንቅለ መንግሥት መሪው ጄኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ በአገሪቱ የደኅንነት እጦት እና ሙስና ተንሰራፍቷል እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ችግሩ ሕዝቡን አማሯል በማለት ነው ፕሬዝዳንቱን ገልብጠው እራሳቸውን ሾመዋል።
በኒጀር መፈንቅለ መንግሥት ከተፈጸመ በኋላ ምዕራባውያን ክስተቱን አጥብቀው ተችተዋል። የአውሮፓ ሕብረት ከአገሪቱ ጋር የነበረውን ሁሉንም አይነት የደኅንነት ትብብር ማቋረጡን ሲያስታውቅ፤ ናይትድ ስቴትስ ደግሞ መፈንቅለ መንግሥት ለመፈጸሙት እውቅና አልሰጥም ከማለቷ በተጨማሪ መፈንቅለ መንግሥት ለተፈጸመባቸው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዙም “የማይናወጥ ድጋፍ አለኝ” ብላለች።
በተመሳሳይ የቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ለኒጀር አደርግ የነበረውን እርዳታ እና የበጀት ድጋፍ አቁሜያለሁ ብላለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የመፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊዎች ለጦሩ አባላት ድጋፋቸውን ለመግለጽ በመዲናዋ ከሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ ፊት ለፊት በውጣት ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ኤአፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው ሰልፈኞቹ “ረዥም ዕድሜ ለሩሲያ”፣ “ረዥም ዕድሜ ለፑቲን”፣ “ውድቀት ለፈረንሳይ” የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ነበር።
በሳህል ቀጠና የሽብርተኝነት መስፋፋትን ለመቆጣጠር ከምዕራባውያን አገራት ጋር በመተባበር ጽንፈኛ እስላማዊ ቡድኖችን ስትዋጋ በቆየችው ኒጀር መፈንቅለ መንግሥት መፈጸሙ የቀጠናውን ደኅንነት ችግር ውስጥ ሊከት እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
“ኒጀር ሽብርተኝነትን በመዋጋት ቁልፍ ሚና እየተጫወተች ነው። ኒጀር ይህ ሚናዋን የምታቆም ከሆነ አሸባሪዎች በቀጠናው እንዲስፋፉ ዕድል ይሰጣል” በማለት ዶ/ር ሌዮናርዶ ሳንቶስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኢኮዋስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መፈንቅለ መንግሥትን በመቃወም ወታደራዊ አማራጭን ልጠቀም እችላለሁ ሲል ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
እአአ 2017 ላይ የቀድሞ የዘ ጋምቢያ መሪ ያያህ ጃሜህ በምርጫ ተሸንፈው ስልጣን አለቅም ሲሉ የሴኔጋል ወታደሮችን ወደ አገሪቱ አዝምቶ ነበር።
ከኒጀሩ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ የቻድ ፕሬዝዳንት መሐማት ኢድሪስ ዴባይ አትኖ ወደ ኒያሜ አቅንተው ወታደራዊ ቡድኑ ስልጣኑን እንዲለቅ ተናግረዋል ብሏል የቻድ መንግሥት።
የምዕራብ አፍሪካ መሪዎች ኒጀርን የተመለከተ በአስቸኳይ ተፈጻሚ የሚሆን ሌሎች ጥብቅ ውሳኔዎችንም አሳልፈዋል።
በኒጀር የአየር ክልሎች ላይ አውሮፕላኖች እንዳይበሩ፣ ከአገሪቱ ጋር የሚያዋስኑ ሁሉም የየብስ ድንበሮች እንዲዘጉ እና መፈንቅለ መንግሥት በፈጸሙት ግለሰቦች ላይ የፋይናንስ ማዕቀብ እንዲጣል አዘዋል።
አሁን ላይ ምዕራባውያን አገራት በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙት የጦር ጄኔራል ከየትኞቹ አገራት ጋር ወዳጅነት ይመሰርታሉ የሚለውን በትኩረት እየተመለከቱ ነው።
መፈንቅለ መንግሥት ተፈጽሞባቸው በወታደራዊ አገዛዝ ሥር የሚገኙ የኒጀር ጎረቤት አገራት ቡርኪና ፋሶ እና ማሊ ፊታቸውን ወደ ሩሲያ አዙረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር በኒጀር የተፈጸመውን መፈንቅለ መንግሥት ትልቅ ድል ነው ሲል ገልጾታል።
የቫግነር መሪ ዬቭጌኒ ፕሪጎዢ “በኒጀር የሆነው ነገር የኒጀር ሕዝብ በቅኝ ገዚዎቻቸው ላይ ያደረጉት ትግል ነው። . . . ዛሬ ነጻነታቸውን እያገኙ ነው” ስለማለታቸው ከቡድኑ ጋር ቅርበት ያለው የቴሌግራም ቻናል ገልጿል።
ቫግነር በመካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ እና ማሊ ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በአፍሪካ አሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን አብዛኛውን ግዜ በየአገራቱ የሚገኙ የማዕድን ማውጫ ስፍራዎችን በመቆጣጠር በንግድ ሥራ ላይ ይሰማራል።