ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያ የአዳዲስ ቀረጦች የአደባባይ ተቃውሞ አንድ ወጣት በጥይት መገደሉ ሕዝባዊ ቁጣ ቀሰቀሰ
የኬንያ መንግሥት ሊጥለውን ያሰባቸውን ቀረጦች በመቃወም አደባባይ በወጡ ሰልፈኞች ላይ በተከፈተ ተኩስ አንድ ወጣት በፖሊስ ተገደለ።
አገር አቀፍ በሆነው ተቃውሞ ላይ የ29 ዓመቱ ወጣት ህልፈት ሕዝቡን አስቆጥቷል።
ሬክስ ካንይኬ የተሰኘው ወጣት በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ ማለፉን በመዲናዋ ናይሮቢ የሚገኝ አንድ ሆስፒታል ዶክተር ለኬንያ ጋዜጣ ተናግረዋል።
የኬንያ የፓርላማ አባላት የተለያዩ ቀረጦችን በያዘቀው ረቂቅ የፋይናንስ ሕግ ላይ እየተከራከሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
ፖሊስ በፓርላማ አቅራቢያ ላይ ለተቃውሞ በተሰበሰቡ ሰልፈኞች ላይ አስለቃሽ ጭስ እና ውሃ በመርጨትም ለመበተን ሞክሯል።
ሐሙስ ዕለት ከ100 በላይ ተቃሚዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወቀው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ፖሊስ ያልተመጣጠነ ኃይል እየተጠቀመ ነው ሲል ከሷል።
ማክሰኞ ዕለት “ፓርላማን እንቆጣጠር” (ኦኩፓይ ፓርላመንት) በሚል የተጀመረው የአደባባይ ተቃውሞ የሕዝባዊ እምቢተኝነቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል መንግሥት አንዳንድ አወዛጋቢ ቀረጦችን እንዲሰርዝ አስገድዶታል።
ከዚህም ውስጥ ዳቦ ላይ እስከ 16 በመቶ የሚደርስ እና በተሽከርካሪዎች ላይ 2.5 በመቶ ሊጣል የነበሩ ቀረጦች ይገኙበታል።
ሆኖም አጠቃላይ የፋይናንስ ሕጉ እንዲሰረዝ እየጠየቁ ያሉ ወጣቶች ቁጣቸው አልተገታም። ተቃውሞ እና ቁጣቸውን በፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ አጠቃላይ አስተዳደር ላይ አድርገዋል።
ዊልያም ሩቶ ሥልጣን ከተቆጣጠሩ ጀምሮ በርካታ አዳዲስ እና ተቀባይነት ያላገኙ ግብሮችን አስተዋውቀዋል። ይህም የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት እንደሚያኮሰምን እና ሥራ አጥነትን እንደሚያስከትል ተችዎች እየተናገሩ ነው።
ፖሊስ ወጣቱ ተተኩሶበት የተመተባትን ስፍራ እንደጎበኘ እና አሟሟቱንም ለማጣራት ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ወጣቱ በኪሱ ውስጥ ብሔራዊ መታወቂያ ካርዱን እና ስልኩን ብቻ ይዞ እንደነበር እንዲሁም ምንም መሳሪያ አለመያዙን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ቦኒፌስ ምዋንጊ ገልጿል።
የሟቹ እናት ጊሊያን ሙያንኦ ለሲቲዝን ቲቪ እንደተናገሩት ልጃቸው ከሥራ ሲመለስ በጥይት እንደተመታ አስረድተዋል።
“ጥይት በተተኮሰበት ወቅት ፖሊስ እየረጨ የነበረውን አስለቃሽ ጭስ ለመሸሽ እየሞከረ ነበር” ብለዋል። በማዕከላዊ ናይሮቢ በሚገኘው ብሊስ ሆስፒታል ቢወሰድም ሕይወቱ ማለፉን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
“በጥይት የተመታው በጭኑ የላይኛው መካከለኛ ክፍል ላይ ነው። ወደ ሆስፒታላችን ከመድረሱ በፊት በከፍተኛ ሁኔታ ደም ፈሶት ለሞት ዳርጎታል” ሲሉም ዶክተሩ መናገራቸውን ኔሽን የተሰኘው የዜና ድረ ገጽ ዘግቧል።
ከፍተኛ ተቃውሞ እየቀረበበት ያለው ይህ አወዛጋቢ ረቂቅ በፓርላማው የመጀመሪያውን ዙር ያለፈ ሲሆን፣ ሕግ ሆኖ ለመጽደቅ በመጪው ማክሰኞ ድምጽ ይሰጥበታል።
መንግሥት አገሪቱ ያለባትን 80 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብሔራዊ ዕዳ ለመቀነስ የተለያዩ ግብሮችን መጣል አንዱ እርምጃ ነው ይላል።