ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አዲሱ የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ “የሕዝቡን የመክፈል አቅም ታሳቢ ያላደረገ ነው” የሚል ትችት በምክር ቤት አባላት ቀረበበት
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው አዲሱ የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ፤ “ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ላይ ጫና የሚፈጥር ነው” የሚል ትችት ከምክር ቤት አባላት ቀረበበት።
ሁለት የምክር ቤት አባላት መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያወጣቸው ተደራራቢ የታክስ ረቂቅ አዋጆች እና ማሻሻያዎች “የሕዝብን የመክፈል አቅም ታሳቢ ያደረጉ አይደሉም” ሲሉ ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 13/2016 ዓ.ም. የቀረበለትን የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር ዕይታ ለፕላን፣ ፋይናንስ እና በጀት ጉዳዮች መርቶታል።
ምክር ቤቱ ረቂቁን ለቋሚ ኮሚቴው የመራው በሦስት ተቃውሞ እና በአብላጫ ድምጽ ነው።
ረቂቁ ለዝርዝር ዕይታ ወደ ቋሚ ኮሚቴው ከመመራቱ በፊት በተካሄደ ውይይት ላይ አምስት የምክር ቤት አባላት አስተያየታቸውን ለመስጠት ዕድል አግኝተዋል።
ይህን ዕድል ካገኙ የምክር ቤት መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር አወቀ ሃምዛዬ፤ ምክር ቤቱ እያጸደቃቸው ያሉት የታክስ አዋጆች “የደኽየውን እያደኽዩ የሚሄዱ [ናቸው]” ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር አወቀ አክለውም “ድሃው ላይ ነው እየጨመርን፤ ታክሶች እያጸደቅን ያለነው” ብለዋል።
የምክር ቤት አባሉ ለዚህ ማሳያነት ያነሱት ከዚህ በፊት በምክር ቤቱ የጸደቁ እና ውይይት እየተደረገባቸው ያሉ የታክስ አዋጆችን ነው።
ዶ/ር አወቀ “ከዚህ በፊት ያጸደቅናቸውን [የታክስ] አዋጆችን ጨምሮ አሁን ያለው የአገራችን ሁኔታ ሲታይ በጣም ችግር ውስጥ ነው ያለው” ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ የቴሌኮም አገልግሎቶች 5 በመቶ የኤክሳይስ ታክስ እንዲጣልባቸው ያደርጋል።
በተመሳሳይ ከአንድ ወር በፊት ለፓርላማ ቀረበው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ የኤሌክትሪክ እና የውሃ አገልግሎት በገደብ ቫት ይከፈልባቸዋል።
ዶ/ር አወቀ በዛሬው የፓርላማ ንግግራቸው ላይ ይኼንኑ የተደራራቢ ታክስ ጉዳይ “ቫት ተጨመረ፤ ነዳጅ ላይ ተጨመረ፤ ይኼ እንዴት ነው የሚጣጣመው?” ሲሉ በጥያቄ መልክ አንሰተውታል።
“ድሃው በጣም እየጮኸ ነው” ያሉት ዶ/ር አወቀ፤ “ታክስ ሲጣል ተጠቃሚ ላይ ነው ዞሮ ዞሮ የሚወድቀው። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምናየው ሃብታሞች አይከፍሉም፤ ባለንብረቱ አይከፍልም። ታክስ ድሆች ናቸው የሚከፍሉት” ሲሉ በተደራራቢ ታክስ ምክንያት ጫና ላይ የሚወድቁት “ድሆች” መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
የምክር ቤት አባሉ አክለውም “ሌላስ ይሄ ድሃ [ሕዝብ] ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ ታስቧል ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ሌላኛው ረቂቅ አዋጁ ላይ ጠንከር ያለ አስተያየት የሰጡት ተቃዋሚውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቡት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ናቸው።
ዶ/ር ደሳለኝ “እኔ ይሄ የንብረት [ታክስ] አዋጅ መጽደቅ የለበትም ብዬ ነው የምከራከረው” ብለዋል።
የምክር ቤት አባሉ አክለውም፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን [የንብረት ታክስ] የመክፈል አቅም የለውም። አሁን ባሉ ተደራራቢ ታክሶች እና የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ደረጃ ኢትዮጵያውያን የንብረት ታክስን የሚከፍሉበት አቅም አላቸው ብዬ አላስብም እና እንዲታይ ምክር ቤቱን መማጸን እፈልጋለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ዶ/ር ደሳለኝ መኖሪያ ቤት የሚገነባው “በሕይወት ዘመን” ውስጥ መሆኑን በማንሳት ፤ “[አንድ ሰው] በሕይወት ዘመኑ ሠርቶ ከሚያገኘው ንብረት ላይ መንግሥት እንዴት ታክስ ለመሰብሰብ ያስባል? አይከብድም ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል።
የንብረት ታክስ መጣል አስፈላጊነትም በዶ/ር ደሳለኝ ትችት ቀርቦበታል።
ቢቢሲ በተመለከተው የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ “በከተሞች ውስጥ የሚፈራው ቋሚ ንብረት ከጊዜ ወደጊዜ ከከተሞቹ ዕድገት ጋር እየጨመረ በመሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የክልል መንግሥታት ከዚህ ሀብት ተገቢውን ድርሻ በታክስ አማካኝነት እየሰበሰቡ አይደለም” ሲል ያትታል።
ዶ/ር ደሳለኝ በዛሬው የምክር ቤት ውሎ፤ “ይህ የአዋጁ አስፈላጊነት መርኅ መሥራት ያለበት ከመኖሪያ ቤት ውጭ ያሉ ትርፍ የንግድ ህንጻዎች ላይ ነው” ብለዋል።
ከዶ/ር አወቀ እና ዶ/ር ደሳለኝ ውጭ የመናገር ዕድል የተሰጣቸው የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ የሆኑት የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው የንብረት ታክስን ደግፈው አስተያየት ሰጥተዋል።
አዲሱ የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ምን ይዟል?
የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤት በ2015 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ባደረጉት የጋራ ስብሰባ የንብረት ታክስ የመጣል እና የመሰብሰብ ሥልጣን የክልል መንግሥታት እንዲሆን መወሰናቸው ይታወሳል።
የንብረት ታክስን ማዕቀፍ የሚወስን አዋጅ ደግሞ የፌደራል መንግሥት እንዲያወጣ ወስነዋል።
ይህን ውሳኔ ተከትሎ ነው ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ በአዋጁ ማብራሪያ ላይ ሰፍሯል።
ይኸው ማብራሪያ የንብረት ታክስ መጣልን አስፈላጊነት ሲያብራራ፤ “በከተሞች ውስጥ የሚፈራው ቋሚ ንብረት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከከተሞቹ ዕድገት ጋር እየጨመረ በመሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የክልል መንግሥታት ከዚህ ሀብት ተገቢውን ድርሻ በታክስ አማካኝነት እየሰበሰቡ አይደለም” ይላል።
የቋሚ ንብረት ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ “በከፍተኛ ደረጃ” እያደገ መሆኑን ያወሳው ማብራሪያ “ለዚህ የቋሚ ንብረት ዋጋ (እሴት) መጨመር በክልል እና በማዘጋጃ ቤት ደረጃ የሚከናወኑ የመሰረተ-ልማት አቅርቦት ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ” ሲል ያትታል።
በረቂቅ አዋጁ መሰረት የንብረት ታክስ የሚጣልባቸው የንብረት አይነቶች፤ በከተማ ውስጥ በሚገኝ መሬት፤ በመሬት ማሻሻያ እና በህንጻ ናቸው።
“መሬት እና በመሬት ላይ የሚደረግ ማሻሻያ እንዲሁም ህንጻ በተናጠል ተገምተው በተለያየ የማስከፈያ ምጣኔ ታክሱ እንደሚከፈልባቸው” አዋጁ ይደነግጋል።
ይህ አዋጅ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች ላይ ተፈጻሚ ቢሆንም ማብራሪያው “ክልሎች ይህንን አዋጅ መሰረት በማድረግ ከተጨባጭ ሁኔታቸው ጋር በተጣጣመ አኳኋን የየራሳቸውን የንብረት ታክስ ህግ እንዲያወጡ ይጠበቃል” ይላል።
ረቂቅ አዋጁ መሰረት በማንኛውም ከተማ አስተዳደር የሚወጣ የታክስ ማስከፈያ ምጣኔ ከመጽደቁ በፊት “ለ60 ቀናት ያህል ለህዝብ ውይይት እና አስተያየት ክፍት መደረግ አለበት” ሲል ይደነግጋል።
ከንብረት ታክስ ነጻ ስለሚደረጉ የንብረት አይነቶች በረቂቅ አዋጁ ተዘርዝረዋል።
በረቂቁ መሰረት ለአንድ ቤተሰብ መኖሪያነት አገልግሎት እየሰጠ ያለ መኖሪያ ሕንፃ፣ የሐይማኖት ተቋማት ለአምልኮ ተግባር እንዲሁም ለመካነ መቃብር አገልግሎት የሚጠቀሙበት ቦታ እና ሕንፃ፣ እንዲሁም በከተማ ውስጥ ያለ ሙሉ በሙሉ ለግብርና ስር የዋለ መሬት ከታክሱ ነጻ ናቸው።
ረቂቁ የንብረት ታክስ ለመክፈል የሚያስችል የገቢ ምንጭ የሌላቸው ባለንብረቶችን የተመለከተ ድንጋጌ ተካትቶበታል።
በዚህ ድንጋጌ መሰረት “የገቢ ምንጭ የሌላቸው መሆኑ በከተማው አግባብ ያለው የመንግስት አካል የተረጋገጠ ግለሰቦች ሊከፍሉት የሚገባውን የንብረት ታክስ የመኖሪያ ቤቱን በሽያጭ ወይም በሌላ ማናቸውም መንገድ ለሶስተኛ ወገን በሚያሰተላልፉበት ጊዜ ለመክፈል የግዴታ ስምምነት እንዲፈርሙ ሆኖ፤ ክፍያው እንዲዘገይ ሊደረግ ይችላል”