ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፌደራል መንግሥት በኤሌክትሪክ እና በውሃ አገልግሎት ላይ ቫት የሚጥል ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ አቀረበ
የኤሌክትሪክ እና የውሃ አገልግሎት በገደብ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) እንዲከፈልባቸው የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።
ትናንት ማክሰኞ ግንቦት 6፤ 2016 ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከታክሱ ነጻ የሚሆኑት የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ ከሚወሰን በታች የኤሌክትሪክ እና ውሃ ፍጆታ ያላቸው ናቸው።
አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ሲጸድቅ ለሁለት አስርት ዓመታት በስራ ላይ ቆየውን የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ እና ከዛ በኋላ እሱን ለማሻሻል ሁለት ጊዜ የወጡትን የማሻሻያ አዋጆች ሙሉ በሙሉ የሚሽር ነው።
“አነስተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ያለበትን ወጪ ለማርገብ ሲባል” የኤሌክትሪክ እና የውሃ አገልግሎት ከታክሱ ነጻ ተደርገው እንደነበር የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ላይ ሰፍሯል።
በስራ ላይ ያለው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ከ20 ዓመት በፊት በ1994 ከወጣ በኋላ ለሁለት ጊዜያት ያህል ማሻሻያ ተደርጎበታል።
የመጀመሪያው ማሻሻያ የተደረገው ከ15 ዓመታት በፊት በ2001 ዓ.ም ነው። ሁለተኛው ማሻሻያ ደግሞ የተደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በ2011 ዓ.ም. ነው።
እነዚህ ሁለት ማሻሻያዎች ቢደረጉም በስራ ላይ ያለው አዋጅ “በኢኮኖሚ እንቅስቃሴላይ በመደረግ ላይ ያሉ ለውጦችን ተከትሎ የተሟላ ማሻሻያ ሳይደረግበት” 20 ዓመታት ማስቆጠሩን የአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ ይገልጻል። ማብራሪያው አክሎም “ጊዜውን የዋጀ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል” ሲል አዋጁን በአዲስ አዋጅ ለመተካት ያስፈለገበትን ምክንያት አስፍሯል።
ረቂቅ አዋጁ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ የመሆን መብት ላይ ማስተካከያዎችን አድርጓል።
ረቂቁ ማብራሪያ “የተጨማሪ እሴት ታክስ ከሚታይበት ጉድለት አንዱ እና ዋነኛው በርካታ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ከታክሱ ነጻ መደረጋቸው ነው” ይላል።
“ከታክሱ ነጻ የተደረጉ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ዋነኛ ዓላማ ታክሱ ዝቅተኛ ገቢ ባለው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ጫና መከላከል እና የወጪ ንግድን ማበረታት” መሆኑን የጠቀሰው ማብራሪያ “ሁሉም ሰው ከታክሱ ነጻ በመሆኑ ዓላማውን ስቷል” ሲል ያትታል።
በረቂቅ አዋጁ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ በማድረግ የተሰጠውን “ልዩ መብት” እንደገና በመፈተሽ ማስተካከያዎች መደረጋቸውን ማብራሪያው ይገልጻል።
ከእነዚህ ማስተካከያዎች መካከል “ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ ደርገው ከነበሩት [ዕቃዎች እና አገልግሎቶች] መካከል በቂ ምክንያት ያልተገኘላቸው ታክሱ እንዲከፈልባቸው ማድረግ” አንዱ ነው።
ከታክስ ነጻ ተደርገው አሁን ታክስ እንዲከፈልባቸው ከተደረጉ አግልግሎቶች መካከል የውሃ እና ኤሌክትሪክ እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎቶች ይገኙበታል።
በስራ ላይ ያለው አዋጅ የኤሌክትሪክ፣ የኬሮሲን [ናፍጣ] እና የውሃ እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎትን ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ እንዲሆኑ እድርጎ ነበር።
ይህን አዋጅ የሚሽረው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ግን የውሃ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ እና የትራንስፖርት አገልግሎቶች በገደብ ታክስ እንዲከፈልባቸው አድርጓል።
“ኤሌክትሪክ እና ውሃ በብዛት የሚጠቀመው የመክፈል አቅም ያለው የማህበረሰብ ክፍል” መሆኑን የጠቆመው የአዋጁ ማብራሪያ’ አገልግሎቶቹ ከታክስ ነጻ በመሆናቸው “ይበልጥ ተጠቃሚ የሆነው ይህ የህብረተሰብ ክፍል ነው” ሲል ያትታል። ማብራሪያው አክሎም “ይህ የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ታክሱ የሚያስከትልበት የወጪ ጫና የሌለ በመሆኑ ድጋፉ ትርጉም ያለው አይደለም” ይላል።
የረቂቁ ማብራሪያ “ድጋፉ ታሳቢ ያደረገውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ በሚጠቅም መልኩ ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል” ሲል የውሃ እና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ታክስ እንዲከፈልባቸው ማድረግ ያስፈለገበትን አመክንዮ ያስረዳል።
በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ የውሃ እና ኤሌክትሪክ አገልግሎቶች የተጨማሪ እሴት ታክስ እንደሚከፈልባቸው ቢደነግግም ገደብንም አብሮ ያስቀምጣል። ማብራሪያው፤ “ከታክሱ ነጻ የመሆን መብት ተጠቃሚ የሚሆኑት የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ ከሚወሰን በታች የኤሌክትሪክ እና ውሃ ፍጆታ ያላቸው እንዲሆኑ ተደርጓል” ሲል ገደቡን ያብራራል።
ከታክስ ነጻ የሆኑ አቅርቦቶችን የሚዘረዝረው እና በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የተካተተው ሠንጠረዥ፤ “ሚኒስትሩ በሚያወጣው መመሪያ ከሚወሰን ወርሃዊ ፍጆታ ያልበለጠ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የታሸገ ውሃን ሳይጨምር የውሃ አቅርቦት” ከታክስ ነጻ መሆናቸውን ያትታል።
ከተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ነጻ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎትም በተመሳሳይ በረቂቅ አዋጁ ቅድመ ሁኔታ ላይ ላይ የተመሰረተ ታክስ እንዲከፈልበት ተደርጓል። በአዲሱ ረቂቅ መሰረት ከታክስ ነጻ የመሆን መብት ባለሶስት እግርን ባጃጆችን ሳይጨምር ከስምንት መቀመጫ በታች ያላቸውን ሌሎች ተሽከርካሪዎች እንዳይመለከት ተደርጓል።
ረቂቅ አዋጁ የትራንስፖርት አገልግሎት ከታክሱ ነጻ እንዲሆን የተደረገው፤ “አነስተኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ ክፍል ለትራንስፖርት የሚያወጣው ወጪ እንዳይንር እንዲሁም በጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ የሚከፈለው ታክስ ዕቃዎችን ዋጋ መናር እንዳያስከትል” ለማድረግ እንደነበር ያትታል።
ማብራሪያው አክሎም፤ “ከህዝብ ትራንስፖርት ውጪ ለሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎቶች የዚህ አይነቱን ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ባለመሆኑ” ማሻሻያው መደረጉን ያስረዳል።
ሌላው ረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ ያደረገበት ጉዳይ የታክስ መክፈያ ጊዜ ነው። በ2011 ዓ.ም. የተደረገው የአዋጁ ማሻሻያ ዓመታዊ ግብይታቸው ከ70 ሚሊዮን ብር በታች የሆነ ግብር ከፋዮች የሰበሰቡትን ታክስ የሚያስታውቁት እና የሚከፍሉት በየሶስት ወሩ እንዲሆን ተደርጎ ነበር።
አዲሱ ረቂቅ ይህን የመከፍያ ጊዜ በመሻር “ሁሉም ታክስ ከፋዮች የሰበሰቡትን ታክስ በየ30 ቀኑ እንዲያስታውቁ እና እንዲከፍሉ” አድርጓል። የረቂቁ ማብራሪያ የዚህን ማሻሻያ አመክንዮ ሲያስረዳ “ታክስ ከፋዮች በእጃቸው የሚቆየው ገንዘብ እየበዛ ስለሚያጓጓቸው እንዲሁም ሰርተንበት እንከፍላለን በሚል ምክንያት የሰበሰቡትን ገንዘብ ገቢ ስለማያደርጉ ለከፍተኛ ውዝፍ የታክስ እዳ እንዲጋለጡ ምክንያት ሲሆን ይታያል” ይላል።
የረቂቁ ማብራሪያ “ከ20 ዓመታት በላይ በስራ ላይ የቆየው አዋጅ የነበሩበትን ጉድለቶች የሚያርም እና ታክስ ከፋዩ ህብረተሰብ በቀላሉ ሊረዳው እና ሊፈጽመው የሚያስችል ነው” ሲል አዲሱን ረቂቅ አዋጅ ይገልጸዋል።