ከሕዝቡ ተቃውሞ የገጠመው የኬንያ መንግሥት የተለያዩ ቀረጦችን እንዲቀሩ አደረገ

የኬንያ መንግሥት በተለያዩ ምርቶች ላይ ሊጥል የነበረው ቀረጥ ከሕዝብ በገጠመው ከፍተኛ ተቃውሞ ምክንያት እንዲቀሩ አደረገ።

መንግሥት ተግባራዊ ሊያደርገው የነበረው የፋይናንስ ሕግ እንደ ዳቦ ባሉ ምርቶች ላይ እስከ 16 በመቶ የሚደርስ ጭማሪን የሚያደርግ ነበር።

ረቂቅ ሕጉ ለአገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት ከተላከ በኋላ ኬንያውያን ወደ ምክር ቤቱ በማቅናት ጠንካራ የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ማክሰኞ ሰኔ 11/2016 ዓ.ም. ፖሊስ ከፓርላማው ደጃፍ የተሰበሰቡ ተቃዋሚዎችን በአስለቃሽ ጭስ ሲበትን የምክር ቤት አባላት በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት ሲያደርጉ ነበር።

ማክሰኞ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የሕግ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ተቃዋሚዎቹ ወደ ታሰሩበት አምርተው እንዲፈቱ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

እአአ 2022 ላይ ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ አገሪቱን ካለችበት የ80 በሊዮን ዶላር ዕዳ ለማውጣት እና ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በሚሉ ምክንያቶች የተለያዩ ግብሮችን ተግባራዊ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በዚህም በኬንያውያን ዘንድ ‘ዘኪዮስ’ የሚል ስያሜን አግኝተዋል።

በክርስትና አማኞች ዘንድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዘኪዮስ የሚባል ስግብግብ ቀራጭ አለ።

ፕሬዝዳንቱ “ዘኪዮስ” የሚለውን ስም ያገኙት ፕሬዝዳንት ሆነው ከመጡ ወዲህ በርካታ የግብር አይነቶችን በማስተዋወቅ እና ቀድሞ የነበሩት ላይ ጭማሪ በማድረግ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የገቡትን ቃል የካዱ መሪ ናቸው በሚል ነው።

ፕሬዝዳንቱ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተቀባይነት እና የአገሪቱ አጠቃላይ ገቢ ጭማሪ ቢያሳይም፤ ኬንያውያን ግን ሩቶ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ኑሮ ከብዶናል በማለት ያማርራሉ።

ማክሰኞ ዕለት በነበረው ሰልፍም “ሩቶ ከስልጣን ይውረድ” የሚሉ መፈክሮች በስፋት ተሰምተዋል።

መንግሥት ተግባራዊ ሊያደርገው የነበረው የፋይናንስ ረቂቅ ሕግ ውድቅ መደረጉን የምክር ቤቱ የፋይናንስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፕሬዝዳንቱ በተገኙበት ይፋ አድርገዋል።

የፋይናንስ ኮሚቴ ሰብሳቢው ኩሪያ ኪማኒ ረቂቅ ሕጉን በተመለከተ የሕዝብ አስተያየት መሰብሰባቸውን እንዲሁም ሕጉ ተግባራዊ ቢደረግ በኬንያውያን ላይ የኑሮ ውድነት ያስከትላል በማለት ረቂቅ ሕጉ ውድቅ የተደረገበትን ምክንያት አብራርተዋል።

ይህ ረቂቅ የፋይናንስ ሕግ በዳቦ፣ በምግብ ዘይት፣ በተሸከርካሪዎች እንዲሁም በሞባይል ገንዘብ ማስተላለፊያ ታሪፍ ላይ ጭማሪ ያደርግ ነበር።

ብዙዎች ረቂቅ ሕጉ ተግባራዊ ቢደረግ የልጆች ዳይፐር፣ የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያ፣ የኮምፒዩተር እና የሞባይል ስልኮችን ዋጋ የማይቀመስ ያደርገዋል ብለዋል።

የምክር ቤት አባሉ ኪማኒ ከውጪ በሚገቡ ምርቶች ላይ ግብሩ እንደሚጣል ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ ረቂቅ ሕጉ ውድቅ ከተደረገባቸው በኋላ እስካሁን ያሉት ነገር የለም። ይሁን እንጂ የፋይናንስ ረቂቅ ሕጉ ውድቅ መደረጉ ለአስተዳደራቸው እንደ ትልቅ ውድቀት ተደርጎ ተቆጥሯል።

ፕሬዝዳንቱ ግን ከዚህ ቀደም ባደረጉት ንግግር ኬንያውያን ተጨማሪ ግብርን ለመከፍል ፍቃደኛ እንዲሆኑ አሳስበዋል፤ እንደውም ፕሬዝዳንቱ ኬንያውያን በሚገባቸው ልክ ግብር እየከፈሉ አይደለም ብለዋል።

ሩቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ካለው ዘኪዮስ ጋር መነፃፀራቸው ብዙም እንዳላሳሰባቸውም ተናግረዋል።