ስደተኞች ኢትዮጵያውያን በሚሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ላይ እንዲቀጠሩ የሚፈቅድ ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ

በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች “በኢትዮጵያውያን ሊሸፈኑ በማይችሉ” የሥራ መስኮች ላይ ብቻ እንዲቀጠሩ የሚደነግገውን ሕግ የሚቀይር ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ።

ረቂቁ፤ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂን ለመቅጠር የሚፈልግ ተቋም፤ ተቀጣሪው ግለሰብ “የተለየ ክኅሎት እንዳለው ማስረዳት ሳይጠበቅበት” ፈቃድ እንዲያገኝ የሚፈቅድ ነው።

በ2012 ዓ.ም. የወጣውን እና በሥራ ላይ የሚገኘውን መመሪያ የሚተካው አዲሱ ረቂቅ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ የሚገኙትን ከ900 ሺህ በላይ ስደተኞችን ጉዳይ የሚመራው የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ነው። በረቂቁ ዝግጅት ላይ “ጉዳዩ በቀጥታ የሚመመለከታቸው” የተባሉት ንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር፣ ሥራ እና ክኅሎት እንዲሁም የገቢዎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንደተሳተፉም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በሥራ ላይ የሚሰማሩበትን ሥርዓት የሚዘረጋው ይህ ረቂቅ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት “እውቅና ያገኙ በካምፕም ሆነ ከካምፕ ውጪ ያሉ ስደተኞችን” የሚመለከት እንደሆነ የተቋሙ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ ረቂቅ የተዘጋጀው፤ በሥራ ላይ ያለው መመሪያ “የነበሩበትን ክፍተቶች ማረም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ” መሆኑን ተቋሙ አስታውቋል። የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት፤ ታይተዋል ካላቸው ክፍተቶች ውስጥ አንዱ በ2011 ዓ.ም. በወጣው የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ላይ ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የተሰጡ “መብቶችን በሙሉ” አለመያዙ ነው።

ከእነዚህ መብቶች አንዱ በሥራ ላይ ያለው መመሪያ ዕውቅና ያላቸው ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች እንዲሰማሩ የፈቀደበት የሥራ መስክ እንደሆነ ምንጩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት የወጣው የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ፤ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በቅጥርም ሆነ ግል ሥራ ላይ ሲሰማሩ “ለውጭ አገር ዜጎች ከተሰጡ መብቶች የተሻለውን” እንዲያገኙ እንደሚደረግ ይደነግጋል።

አዋጁ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በሥራ ላይ እንዲሰማሩ ቢፈቅድም በተወሰኑ ዘርፎች መሥሪያ ቤቶች ውስጥ መቀጠር እንዳይችሉ ደንግጓል። በአዋጁ ክልከላ የተቀመጠው፤ “በአገር መከላከያ፣ በአገር ደኅንነት ወይም በውጭ ጉዳይ እና መሰል የፖለቲካ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች” ላይ ነው።

ይህንን አዋጅ ተከትሎ የወጣው መመሪያ ግን የቅጥር ሁኔታ ሲደነግግ ስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎችን የተመለከታቸው “እንደ ውጭ ዜጋ” እንደሆነ ምንጩ አስረድተዋል። ምንጩ፤ “ምንም እንኳ ስደተኞች የውጭ ዜጎች ቢሆኑም ወደ አገር ውስጥ የሚመጡት ባልታሰበ ሁኔታ ተፈናቅለው ነው” ሲሉ ፓስፖርት እና ቪዛ አግኝት ከሚመጡ የውጭ አገር ዜጎች ጋር ያላቸውን ልዩነት አስረድዋል።

ነባሩ መመሪያ የሥራ ፈቃድ አሰጣጥን በሚመለከተው ክፍሉ ላይ አንድ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ ተቀጥሮ ለመሥራት የሚያስችል ፈቃድ ማግኘት የሚችለው “ፈቃድ የተጠየቀበት ስራ በኢትዮጵያውያን ሊሸፈን የማይችል መሆኑ” ሲረጋገጥ እንደሆነ አስቀምጧል። ቀጣሪዎችም፤ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂን ለመቅጠር ፈቃድ የሚያገኙት “በኢትዮጵያውያን ሊሸፈን በማይችል የሥራ መስክ ላይ” እንደሆነ ይገልጻል።

በግል ሥራ ላይ ስለመሰማራት በሚያትተው የመመሪያው ክፍል ላይ ደግሞ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በተናጠል እና በቡድን ፈቃድ አውጥተው መሥራት የሚችሉት “የውጭ አገር ዜጎች ሊሰማሩ በሚችሉባቸው የሥራ መስኮች ላይ” እንደሆነ አስፍሯል።

የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ያዘጋጀው አዲሱ ረቂቅ መመሪያ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የግል ሥራ ስምሪት ላይ የተቀመጠውን ገደብ ቀይሮታል። በረቂቁ መሠረት ስደተኞች ወይም ጥገኝነት ጠያቂዎች እንዳይሠሩ፣ በግል እንዳይሰማሩ የሚከለከሉት “በጠረፍ ንግድ እና ለውጭ አገር ዜጎች የተሻለ መብት በሚሰጡ ሕጎች ለኢትዮጵያውያን ብቻ ከተፈቀዱ የንግድ መስኮች” ላይ ነው።

በተመሳሳይ የስደተኛ እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን የቅጥር ሥራ ፈቃድ ላይ ረቂቁ ለውጥ አድርጓል። በነባሩ መመሪያ ላይ ለስደተኛ እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ቅጥር ላይ ተቀምጦ የነበረው “በኢትዮጵያውያን ሊሸፈን በማይችል የሥራ መስክ” የሚል ቅድመ ሁኔታ በአዲሱ ረቂቅ ላይ አልተካተተም።

ረቂቁ፤ “በአዋጁ ባልተከለከሉ የሥራ መስኮች ላይ” ተቀጥረው መሥራት የሚፈልጉ እውቅና ያላቸው ስደተኛ እና ጥገኝነት ጠያቂዎች “ከሥራ እና ክኅሎት ሚኒስቴር ወይም ሕጋዊ ውክልና ከተሰጠው አካል የሥራ ፈቃድ ማውጣት” እንደሚችሉ ይገልጻል።

ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂን ቀጥረው ማሠራት የሚፈልጉ መሥሪያ ቤቶችም ከመንግሥት የሥራ ፈቃድ ሲያወጡ “ተቀጣሪው የተለየ ክኅሎት እንዳለው ማስረዳት” እንደማይጠበቅባቸው በረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

በረቂቁ መሠረት ስደተኞች እና ጥገኝት ጠያቂዎች የቅጥር ሥራ ፈቃድ ለማውጣት ማቅረብ የሚጠበቅባቸው የግል ታሪክ የተሞላበት የሥራ ፈቃድ መጠየቂያ ቅጽ፣ ከአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የተሰጠ ማንነቱን የሚገልጽ ማስረጃ እና ፎቶግራፍ ነው።

አሠሪዎች የቅጥር ፈቃድ ለማግኘት የሥራ ፈቃድ ጥያቄ ማመልከቻ፣ የተቀጣሪው የግል ታሪክ የተሞላበት ቅጽ እንዲሁም ለሥራ ቅጥር ቃል የተገባ መሆኑ ወይም የሥራ ቅጥር ውል የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

ግለሰቡን የሚያሰማሩበት የሥራ መስክ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የሚጠይቅ ከሆነ ደግሞ “አግባብነት ካለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት የተሰጠ የብቃት ማረጋገጫ” ማቅረብ በተጨማሪ መስፈርትነት ተቀምጧል።

ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚያገኙት የሥራ ፈቃድ በየዓመቱ የሚታደስ እንደሆነ መመሪያው ላይ ተጠቅሷል።

ቀጣሪዎች ስደተኛን ወይም ጥገኝነት ጠያቂን ለማሠራት ፈቃድ የሚያገኙት “ለአንድ የሥራ መደብ ብቻ” እንደሆነም በረቂቁ ላይ ሰፍሯል። ፈቃዱን ካገኙ በኋላም ስደተኛው ወይም ጥገኝነት ጠያቂው “በተፈቀደለት የሙያ መስክ ላይ ብቻ የማሠራት” ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

ግለሰቡ ከሥራ ቦታ ከጠፋ፣ የሥራ ውሉ ከተቋረጠ እንዲሁም የሥራ ቦታ ከቀየረ በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ለመንግሥት የማሳወቅም ቀጣሪዎች ላይ ከተጣሉ ግዴታዎች መካከል ናቸው።

በተጨማሪም፤ ተቀጣሪው ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ “ከቀላል የትራፊክ ሕጎች ውጪ የአገሪቱን የወንጀል ሕጎች መጣሱ ሲረጋገጥ” ለመንግሥት በማሳወቅ የሥራ ፈቃዱ እንዲሰረዝ ማድረግ እንዳለባቸውም ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።