ዶናልድ ትራምፕ ‘ልታሰር እችላለሁ’ በሚል ስጋት ለደጋፊዎቻቸው ጥሪ አቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀናት ውስጥ ልታሰር እችላለሁ በማለት ደጋፊዎቻቸው ተቃውሞ ማሰማት እንዲጀምሩ ጥሪ አቀረቡ።
የትራምፕ ጠበቃ ግን ስለእስሩ ከሕግ አስፈጻሚ አካላት ምንም የተነገራቸው ነገር እንደሌለ እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ስጋታቸውን የገለጹት በመገናኛ ብዙኃን የወጡ ዘገባዎችን መሠረት አድርገው መሆኑን ተናግረዋል።
ዐቃቢያነ ሕጎች ዶናልድ ትራምፕ ላይ ክስ ሊመሰረትባቸው የሚችሉባቸውን መንገዶች እየፈለጉ ሲሆን፣ ይህም በሚቀጥለው ሳምንት ሊሆን እንደሚችል ዘገባዎች አመልክተዋል።
ትራምፕ ላይ ክስ የሚመሠረትባቸው ከሆነ በአሜሪካ ታሪክ በወንጀል ክስ የተጠየቁ የመጀመሪያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።
አሁን ክስ ይቀርብባቸዋል እየተባለ ያለው በአውሮፓውያኑ 2016 ለፕሬዝዳንትነት ከመወዳደራቸው በፊት ትውውቅ የነበራቸው አንዲት የወሲብ ቪዲዮ ተዋናይት ምንም ነገር እንዳትናገር በጠበቆቻቸው በኩል ገንዘብ ከፍለዋል በሚል ነው።
የ76 ዓመቱ ትራምፕ በአሁኑ ጊዜ በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ምርመራ እየተካሄደባቸው ሲሆን፣ እስካሁን በየትኛው በኩል ክስ አልተመሠረተባቸውም። እሳቸውም ምንም ጥፋት አልፈጸምኩል በሚል የሚቀርቡባቸውን ውንጀላዎች ይከላከላሉ።
ትራምፕ ክስ ቢመሠረትባቸው እንኳን በድጋሚ ፕሬዝዳንት ለመሆን በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ለመሆን የሚያደርጉትን ዘመቻ እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል ከሩሲያ ጋር አላቸው በተባለው ግንኙነት እና ፍሎሪዳ ውስጥ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ ምስጢራዊ ሰነዶችን አከማችተዋል በሚል የተደረጉ ምርመራዎች የቀድሞውን ፕሬዝዳንት መነጋገሪያ አድርጓቸዋል።
በሚቀጥሉት ቀናት ትራምፕ ላይ የወንጀል ክስ ይቀርብባቸው እንደሆነ አስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ሊታሰሩ እንደሚችሉ እና ደጋፉፊዎቻቸው ሕዝባዊ ተቃውሞ እንዲያካሂዱ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ ባቀረቡት ተደጋጋሚ ጥሪ ደጋፊዎቻቸው በአሜሪካ ምክር ቤት ሕንጻ ላይ የፈጸሙት ወረራ ታማኝ ተከታዮች እንዳላቸው የሚያሳይ ሲሆን፣ አሁን ያደረጉት ጥሪም ውጥረት እና ግጭትን ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
ቅዳሜ ዕለት ትራምፕ የራሳቸው ንብረት በሆነው ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከማንሃተን ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት “በሕገወጥ መንገድ ሾልከው የወጡ መረጃዎች” ማክሰኞ ዕለት ሊታሰሩ እንደሚችሉ ያመለክታል ብለው ጽፈዋል።
ነገር ግን ዐቃቤ ሕግ እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን አልሰጠም። የትራምፕ ጠበቃ፣ ሱዛን ኔቼልስ እንዳሉት ግን ከሕግ አስፈጻሚ አካላት የደረሳቸው ምንም መረጃ የለም።
የሪፐብሊካን ፓርቲ የምክር ቤት ተወካይ የሆኑት ኬቭን ማካርቲ በትራምፕ ላይ የሚካሄደውን ምርመራ በተመለከተ “ዐቃቤ ሕግ ያለውን ሥልጣን አላግባብ እየተጠቀመ ነው” ሲሉ ተቃውመውታል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንዳሉት በኒው ዮርክ ያሉ ሕግ አስፈጻሚ አካላት በሚቀጥሉት ቀናት የቀድሞውን ፕሬዝዳንት በመክሰስ ፍርድ ቤት ለማቅረብ እየተዘጋጁ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ አሁን ይቀርብባቸዋል ከተባለው ክስ በተጨማሪ የተሸነፉበትን የምርጫ ውጤት በአመጽ ለመቀልበስ በደጋፊዎቻቸው አማካይነት ሙከራ አድርገዋል በሚል ከባድ ክስ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው።
በተጨማሪም ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ የመንግሥት ምስጢራዊ ሰነዶችን በተገቢው መንገድ አልያዙም የሚል እና የተሸነፉበትን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ባለመቀበል በተከሰቱ ቀውሶች ዙሪያ የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ጉዳዩን እየተከታተለ ነው።












