ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ በጓንታናሞ ቤይ ለሁለት አስርት ዓመታት ያቆየችውን አንጋፋ እስረኛን ፈታች
አሜሪካ በጓንታናሞ ቤይ ለሁለት አስርት ዓመታት ያቆየችውን አዛውንቱን እስረኛ ፈታች።
የፓኪስታን ዜግነት ያላቸው የ75 አመቱ ሳይፉላህ ፓራቻ ትናንትና ጥቅምት 19፣ 2015 ዓ.ም ወደ ሃገራቸው ተልከዋል።
በአውሮፓውያኑ 2001 በአሜሪካ ላይ ከደረሰው ጥቃት ከሁለት አመት በኋላ የታሰሩት ግለሰቡ የአልቃይዳ ደጋፊ በሚል ነው።
ሳይፉላህ የአልቃይዳን ታጣቂዎች በገንዘብ በመደገፍ የተጠረጠሩ ሲሆን ክስም ሳይመሰረትባቸው ነው በእስር የቆዩት።
ሳይፉላህ ለአመታትም ንጹህ ነኝ ሲሉም ቆይተዋል።
በአሜሪካ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በኩባ የሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ እስር ቤት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎች የታጎሩበት ነበር።
“በጓንታናሞ ቤይ ታስሮ የነበረው ፓኪስታናዊው ሳይፉላህ ፓራቻ ከእስር ተፈቶ ቅዳሜ ጥቅምት 19፣ 2015 ዓ.ም ፓኪስታን ገብቷል" ሲል የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተናግሯል።
መግለጫው አክሎም “በውጭ አገር ታስሮ የነበረ የፓኪስታን ዜጋ በመጨረሻም ከቤተሰቡ ጋር በመገናኘቱ ደስ ብሎናል” ብሏል።
የሳይፉላህ ጠበቃ ክላይቭ ስታፎርድ-ስሚዝ ደንበኛቸው ለመፈታት ይህን ያህል አመታት የወሰደበትን ምክንያት ጠይቀዋል።
“ከአንድ ዓመት በፊት ነው እንዲለቀቅ የተወሰነው። እናም በዚህ ወቅት ተስፋ በመቁረጥ የኢግልስን ሆቴል ካሊፎርኒያ ይዘፍልንኝ ነበር። የዘፈኑ ግጥም መጎብኘት የምትችለው ነገር ግን መውጣት የማይቻልበትን ሁኔታ የሚያስረዳ ነው” በማለት ክላይቭ ለቢቢሲ ኒውስሃወር ፕሮግራም ተናግረዋል።
ሳይፉላህ በቁጥጥር ስር የዋሉት የአሜሪካው የፌደራል ምርመራ ቢሮ በታይላንድ ውስጥ ባደረገው ዘመቻ ነው።
በአሜሪካ የተማሩት ሳይፉላህ ከአልቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን እና ካሊድ ሼክ መሀመድን ጨምሮ ከአንዳንድ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት አላቸው የሚል ክስ ከአሜሪካ ቀርቦባቸዋል።
መጀመሪያም በአፍጋኒስታን ባግራም በሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ እስር ቤት ከ14 ወራት ቆይታ በኋላ ወደ ጓንታናሞ ቤት እንዲዛወሩ ተደርጓል።
ሚስጥራዊው የአሜሪካ ወታደራዊ እስር ቤት አሜሪካ ከሽብር ጋር በምታደርገው ውጊያ ተጠርጣሪ የሆኑ ሰዎችን ለማጎርና ለማሰቃየት የምትጠቀምበት ነው።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ክስ ያልቀረበባቸው እስረኞችን እንዲፈቱ እንዲሁም ከአልቃይዳ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው ተብለው የተከሰሱ ሰዎች የፍርድ ሂደቱን እንዲያሳልጡም ጥያቄዎች እየበረቱባቸው ነው።