ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፈረንሳይ በመድፈር ወንጀል የተፈረደበት ግለሰብ ይግባኝ ከጠየቀ በኋላ እስራቱ ተራዘመ
በደቡብ ፈረንሳይ የሚገኝ ፍርድ ቤት ዥዜል ፔሊኮን ፍርድ ላይ ይግባኝ የጠየቀው ተከሳሽ ተጨማሪ የአንድ ዓመት እስር ፈረደበት።
የ72 ዓመቷ ዥዜል ፔሊኮን በወቅቱ የትዳር አጋሯ በሆነው ግለሰብ አደናዛዥ ዕጽ ተሰጥቷት ራሷን ስትስት በኢንተርኔት በመለመላቸው ሰዎች ለዓመታት ያስደፍራት ነበር።
የ44 ዓመቱ ሁስሜቲን ዶጋን ምንም እንኳ ለችሎቱ ራሷን ከሳተችው ፔሊኮን ጋር ወሲብ ሲፈጽም የሚያሳይ ቪዲዮ ለችሎቱ ቢቀርብም ነጻ ነኝ ብሎ ተከራክሯል።
ነገር ግን ችሎቱ የግለሰቡን ይግባኝ ውድቅ አድርጎ መጀመርያ ተፈርዶበት በነበረው ዘጠኝ ዓመት ላይ አንድ ዓመት በመጨመር 10 ዓመት እንዲታሰር በይኗል።
ግለሰቡ ባለፈው ታሕሳስ ወር ከሌሎች ጥፋተኛ ከተባሉ 50 ተከሳሾች ጋር የተፈረደበት በመድፈር ወንጀል ነበር።
አቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ የ12 ዓመት ፍርድ እንዲጣል ጠይቆ የነበረ ሲሆን ግለሰቡ ግን እርሱ ራሱ በዶሚኒክ ፔሊኮት "የተያዝኩ" ተጠቂ ነኝ ሲል በችሎቱ ፊት መከራከሪያውን አቅርቧል።
አቃቤ ሕግ በበኩሉ ዶጋን "በግለሰቧ ላይ ላደረሰው ትልቅ ጥፋት"፤ "ኃላፊነት ለመውሰድ ፈቃደኛ አይደለም" ሲል ለችሎቱ አስረድቷል።
ዶጋን ባለፈው ዓመት ጉዳዩ በፍርድ ቤት መታየት ከመጀመሩ አስቀድሞ በቁጥጥር ስር የዋለ ቢሆንም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የተጣለበትን የእስር ጊዜ መፈጸም አልጀመረም ነበር።
ፖሊስ የዥዜል ፔሊኮንን ደፋሪዎች አድኖ በቁጥጥር ስር ያዋለው ዶሚኒክ ፔሊኮን ሰዎቹ ሲደፍሯት ቀርጾ ባስቀረው ቪዲዮ አማካኝነት ነው።
እስር ከተፈረደባቸው 51 ሰዎች መካከል 17ቱ ይግባኝ ብለው የነበሩ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን ይግባኛቸውን አንስተዋል።
ባለትዳር የሆነው ሁሳሜቲን ዶጋን ግን በይግባኙ ገፍቶበታል።
ዶጋን ለፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል ያቀረበው መከራከሪያ ልክ አንደ ሌሎቹ ተከሳሾቹ ሁሉ የዥዜል ፔሊኮንን ከፈቃዷ ውጪ በባለቤቷ አደናዛዥ ዕጽ ተሰጥቷት ራሷን መሳቷን አላውቅም ነበር የሚል ነው።
ጉዳዩን ለመመልከት ለተሰባሰቡ የዳኝነት አባላት (ጁሪ) በመጀመርያው ፍርድ ሂደት የቀረቡ ማስረጃዎች ዳግም ቀርበዋል።
ራሷን የሳተችው ዥዜል ፔሊኮንን ስትደፈር የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ቢቀርቡም ዶጋን ግን በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሴት ብትሆንም እርሷን የመድፈር ምንም ዓይነት ፍላጎት አልነበረኝም ሲል ተከራክሯል።
"ወሲብ ነው የፈጸምኩት፤ ማንንም አልደፈርኩም" ብሏል።
"ለእኔ መድፈር ማለት አንድን ግለሰብ በኃይል ማስገደድ፣ ማሰር፣ አላውቅም . . . እኔ ራሴ የጥቃት ሰላባ ነኝ።"
የዥዜል ፔሊኮን ለፍርድ ቤቱ "እኔ ብቻ ነኝ የጥቃት ሰለባ" ስትል ተናግራለች።
ዥዜል የሰባት ልጆች አያት ናት።
ዥዜልን ባለቤቷ በዕፅ እያደነዘዘ ከ80 በላይ በሚሆኑ ወንዶች ለዓመታት አስደፍሯታል።
ወንዶቹን በበይነ መረብ እየፈለገ፣ ወደ ቤታቸው እየጠራ፣ ባለቤቱ መኝታ ክፍላቸው በተኛችበት ለዓመታት አስደፍሯታል።
ባለቤቱን በተደጋጋሚ ሲደፍርና በማያውቋት ወንዶች ሲያስደፍር የሚያሳዩ በሺዎች የሚቆጠሩ ምሥሎችና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ኮምፒውተሩ ላይ ፖሊስ ካገኘ በኋላ ነበር የፍርድ ሂደቱ የተጀመረው።
ለዓመታት ሲደፍሯት የነበሩ የማታውቃቸው ግለሰቦችና ባለቤቷ ፍርድ ቤት ቀርበው ተፈርዶባቸዋል።
ባለቤቱን ለዓመታት እያደነዘዘ የደፈረው እና ከ50 በላይ በሚሆኑ ወንዶች ያስደፈረው ዶሚኒክ ፔሊኮት የ20 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።