ባለቤቱን ለዓመታት ከ50 በላይ በሚሆኑ ወንዶች ያስደፈረው ፈረንሳያዊ 20 ዓመት ተፈረደበት

ባለቤቱን ለዓመታት እያደነዘዘ የደፈረው እና ከ50 በላይ በሚሆኑ ወንዶች ያስደፈረው ዶሚኒክ ፔሊኮት የተባለው ፈረንሳያዊ በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል።

ግለሰቡ ጄዚል ፔሊኮት የተባለች ባለቤቱን አደንዝዝዞ በመድፈር እና የማያውቋትን ወንዶች በመልመል ለዓመታት በማስደፈሩ የ20 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

ከሱ በተጨማሪ ሌሎች የደፈሯት ግለሰቦች የተለያዩ የእስር ቅጣቶች ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

የ72 ዓመቷ አያት የቀድሞ ባለቤቷን ብያኔ ሲተላለፍ በፍርድ ቤቱ ግድግዳ ላይ ጭንቅላቷን አረፍ እንዳደረገች የቢቢሲ ዘጋቢ ተመልክቷል።

ግለሰቡ ከዚህም በተጨማሪ ከተከሳሾቹ መካከል ዣን ፒየር ማርቻል የተባለውን ግለሰብ በመድፈር እንዲሁም የሴት ልጁን ካሮሊን እና የልጆቹን ባለቤቶች የተጋለጡ ምስሎች በማንሳት ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ጥቃቱ የተፈጸመባት የ72 ዓመቷ ጂዜል ፔሊኮት የፈረንሳይ ሕግ የሰጣትን ማንነቷን የመደበቅ መብቷን በመተው ታሪኳንም ሆነ ራሷን ለሕዝብ ይፋ አድርጋለች።

በፈረንይ ለሰው ህሊና የሚዘገንነው ወንጀል የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

ጄዚል ፔሊኮትን የቀድሞ ባለቤቷ እያደነዘዘ ከ80 በላይ በሚሆኑ ወንዶች ለዓመታት አስደፍሯታል።

ይህም ለአስር ዓመታት ያህል የተፈጸመ ሲሆን፣ ግለሰቡ ባለቤቱን በተደጋጋሚ የደፈረበትን እና የማያውቋትን ወንዶች እያጋበዘ ያስደፈረባቸው ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች ኮምፒውተሩ ላይ ተገኝተዋል።

ግለሰቡ ባለቤቱን የደፈረበት እና ያስደፈረበትን በሺዎች የሚቆጠሩ ፎቶዎች በማንሳት እና ቪዲዮዎችን በመቅረጽ አስቀምጧል።

አነስተኛ በሆነችው በደቡባዊቷ ፈረንሳይ፣ ማዛን የተፈጸመው ይህ ድርጊት በርካቶችን ያንቀጠቀጠ ነው። የድርጊቱን ፈጻሚዎች ሰብዓዊነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ፣ የጭካኔ ጥግን ያጋለጠ እንዲሁም የሰማውን ሁሉ ህሊና የረበሸ ሆኗል።

ግለሰቡ ለዓመታት የባለቤቱን ምግብ እና መጠጥ በጭንቀት መድኃኒት እና በእንቅልፍ እንክብል ሲመርዝ ቆይቷል።

ሚስቱ በየምሽቱ ራሷን ከመሳት በተጨማሪ ጤንነቷ ክፉኛውኑ ተጎድቷል።

ጂዜል ይህንን አስደንጋጭ ሁኔታ የተረዳችው ከአራት ዓመታት በፊት ነው።

ለአምስት አስርት ዓመታት በትዳር አብራው የኖረችው ባለቤቷ ከ80 በላይ የሚሆኑ ወንዶችን በመጋበዝ እንዳስደፈራት እና ድርጊቱን እንደቀረጸው የተረዳችው ከፖሊስ ነው።

በመድፈር ወንጀሉ ላይ የተሳተፉት ወንዶች ቁጥር ብዛት ፈረንሳይን አስደንግጧል።

በቪዲዮው ላይ ከታዩት 83 ወንዶች መካከል ፖሊስ መለየት የቻለው 50ዎቹን ብቻ ነው።

ዕድሜያቸው ከ26 እስከ 68 ሲሆን፣ በተለያዩ ሙያዎች ውስጥ ያሉ ናቸው። የእሳት አደጋ ሠራተኞች፣ ፋርማሲስቶች፣ ነርስ፣ የእስር ቤት ጠባቂ፣ ጋዜጠኞች ተካተውበታል። በርካቶች የልጆች አባት እና ባለትዳሮች ናቸው።

አንደኛው ኤችአይቪ በደሙ እያለ እያወቀ ስድስት ጊዜ እንደደፈራት ፖሊስ ይፋ አድርጓል።

ምንም እንኳን ኤችአይቪ ባይተላለፍባትም ሌሎች በወሲብ በሚተላለፉ በሽታዎች ተይዛ እንደነበር የጤና ባለሙያ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የጤና እክሎች እንደተከሱባት ተገልጿል።

ዶሚኒክ በአንድ ድረ ገጽ ላይ "እሷ ሳታውቅ" ከባለቤቱ ጋር ወሲብ እንዲፈጽሙ አንድ ጽሁፍ መለጠፉን ተከትሎ ነው በርካቶች የመጡት።

ድረ ገጹ በአሁኑ ወቅት የተዘጋ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት 500 ሺህ ጎብኚዎች ነበሩት።

ፖሊስ ባደረገው ምርመራ 4 ሺህ የሚሆኑ ጂሴል የምትደፈርበትን ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች አግኝቷል።

ድርጊቱ ከአውሮፓውያኑ 2011 እስከ 2020 የተፈጸመ ሲሆን፣ 200 ገደማ መደፈሮችን ይዘዋል።

ሁኔታው ይፋ የሆነው ግለሰቡ በአንድ መደብር ውስጥ ተደብቆ የሴቶች ቀሚስ ስር ፎቶ ሲያነሳ በመያዙ ነበር።